መግቢያ
“እንግዲህ ከሁሉ አስቀድሞ ልመናና ጸሎት፣ ምልጃና ምስጋና ለሰዎች ሁሉ፣ ለነገሥታትና ለባለ ሥልጣናት ሁሉ እንዲደረግ አሳስባለሁ፤ ይህም በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወትና በቅድስና ሁሉ፣ በሰላምና በጸጥታ እንድንኖር ነው።” (1 ጢሞ. 1:1-2)
“ጻድቃን ሥልጣን ሲይዙ ሕዝብ ሐሤት ያደርጋል፤ ክፉዎች ሲገዙ ግን ሕዝብ ያቃስታል።” (ምሳ. 29:2)
"አቤቱ ሉዓላዊ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን የሚፈሩ መሪዎች ስጠን"- አሜን!
በጥቅሉ ስናስተውል፣ በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ሊኖር ስለሚገባው መስተጋብር ሁለት ጠርዝ ላይ የቆሙ አመለካከቶች አሉ። አንደኛው፣ ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞውኑ “አያገባትም፣ ገለልተኛ መሆን አለባት” የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ መልእክቷ ፖለቲካዊ ልብስ እንዲለብስ ያደረገ ተቃራኒ ጥግ ነው። የወንጌልን ተልእኮ ወደ ፖለቲካዊ ግዛት ዝቅ ማድረግ፣ የእግዚአብሔርን ዓላማ መሳት ነው። ክርስትና በማኅበራዊ ፍትሕ ጉዳዩች ሊይ ሊኖረው የሚገባውን ዕይታ በማርክሳዊ ርእዮት ዓለም ሊቃኝ የሞከረው ልቅ ነገረ መልኮት (liberation theology) የወደቀበት ፈተና፣ የወንጌልን ተልእኮና ማኅበራዊ ተሃድሶን በተወራራሽነት የመረዳት ስሑት ተልእኮአዊ የራስ ግንዛቤ እንደሆን ልብ ይሏል! በሌላው ጠርዝ ደግሞ፣ የወንጌልን ማኅበራዊ አንድምታ መካድ፣ ኀጢአት ያመጣውን ገለሰባዊና ማኅበራዊ ስብራቶች መካድ ነው። በአገራችን ዐውድ፣ በቤተ ክርስቲያንና መንግሥት መካካል በላው መስተጋብር ውስጥ፣ ጠርዝ የለቀቁ ዕይታዎች ምክንያታቸው ከሁለቱ አንዱ ነው።
በእግዚአብሔር ፍጥረት ውስጥ፣ ኀጢአት ትልቅ ነውጥ ነው። በዘፍጥረት ላይ እንደምናየው፣ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” (ዘፍ 1÷31)። ይህን “እጅግ መልካምነት” በማበላሸት፣ የመስተጋብሮች ሁሉ ስብራት ምክንያት የሆነው ይኸው ኀጢአት ነው። ማኅበራዊ ነውጦቻችን የሚቀዱት፣ በኀጢአት ክፋት ከተበከለው የሰው ልብ ውስጥ ነው። ለኀጢአትና ጦሱ፣ እግዚአብሔር በብቸኛና ምትክ በሌለው የመጨረሻ መፍትሔነት ለዓለም የሰጠው ክርስቶስን ነው - ርእዮተ-ዓለም አይደለም። እርሱ ስለ እኛ ምትክ በመሆን በመስቀል ሞት ከርግማን ዋጀን--“በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል፤ (ገላ 3÷13)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ሞቱ፣ በእግዚአብሔርና በሰው፣ በሰውና በሰው መካካል ያለውን የጥል ግድግዳ አፍርሷል። በመስቀሉ ሥራ ኀጢአት ያመጣው ጠላትነት በመወገዱ፣ የግንኙነት ስብራቶች ታድሰዋል! የታረደው በግ - ክርስቶስ፣ "ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጀ" (ራእ 7:9)። ከመስቀሉ በስተቀር ቤተ ክርስቲያን ሌላ ትምክሕት፣ ክብርም መልእክትም የላትም! ለአይሁድ መሰናከያ፣ ለሮም የእፍረትና የሞኝነት ምልክት የሆነው መሰቀል የቤተ ክርስቲያን ውበት ነው። በአጭሩ - ጥሪዋ፣ ዐላማዋና ስብከቷም ሊሆን የሚገባው ይኸው የመስቀሉ ቤዛዊ ሥራ ብቻ ነው።
ክርስቶስ መጨረሻ፣ ምትክ የሌለውና ዘላለማዊ የእግዚአብሔር መገለጥ በመሆን፣ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም ሰላም ሆኗል ስንል፣ የጥል ግድግዳዎች መፍረሳቸውና ዕርቅ መደረጉን ለመናገር ነው። (ሮሜ 1÷1-4) በቀዳማዊነት፣ የክርስቶስ ተልእኮ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አይደለም (ማኅበራዊ ንቅናቄ መሪ - Social Reformer – ወይም የሞራል መምህር - Moralist አይደለም) የምንልበት ምክንያት፤ ሰው ያጣው የእግዚአብሔርን ሙሉነትና ክብር ስለሆነ ነው። የሰላም ወንጌል፣ ሰው ያጣውን ክብር በክርስቶስ ዎጃዊ ሥራ የመመለሱ የምሥራች ነው (1ጴጥ 2፥24፤ ሮሜ 3:23)። ስለዚህ በየትኛውም መልኩና መለኪያ “ጥሩና የተሻለ የሚባለው ማኅበራዊ መፍትሔ፣ ሰውም ምሉዕ አያደርገም። ሕግ “ነጩና ጥቁርኑ” (በአገራችን ዐውድ ደግሞ ‘ብሔሮችን) በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ያስቀምጥ ይሆናል፤ ሆኖም አንዱን በሌላው ልብ ውስጥ አያስቀምጥም! እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ክርስቶስን በብቸኛ የመጨረሻ መፍትሔነት ለዓለም የሰጠው፣ የክፋት ሁሉ ጉሮኖ የሆነውን የሰው ልጅ ልብ እንዲያው በጸጋው አዲስ ለማድረግ ነው። በዚህ አግባብ፣ ቤተ ክርስቲያን የግራም የቀኝም አይደለችም፤ የክርስቶስ እንጂ። ሕይወቷ፣ ወገንተኝነቷ እንዲሁም ልስኗ ይኸው የክርስቶስ ውንጌል ብቻ ነው።
መስቀሉ ያስገኘው ዕርቅ፣ ማኅበራዊ አንድምታም እንዳለው ድግሞ ልብ ልንል ይገባል። ክርስቲያናዊ ሕይወት ምሉዕ ሕይወት ነው፤ ማለት ከፊሉ ምድራዊ፣ ከፊሉ ደግሞ ሰማያዊ በሚል መደላድል አይከፋፈልም። ሰው ለእግዚአብሔር ክብር እንዲኖር የተፈጠረ በመሆኑ፣ በቀዳሚነት ከእግዚአብሔር ጋር፣ ከዚያ ቀጥሎ እርስ በእርስ ባለው መስተጋብር ለእግዚአብሔር ክብር መኖር የሕይወቱ ግብ ነው። ከዚህ አንጻር፣ “አገራችን በሰማይ ነው፤ በምድር መጻተኞች ነን” የሚለው አባባል በአንድ ጐኑ ብቻ የተወጠረና የተፋለሰ የማንነት ቀውስ ነው። በክርስቶስ የመስቀል ቤዛዊ ሥራ የተገኘው ድነት፣ ሰውን ሁለንተናዊ በሆነ መልክ የሚዋጅ ነው። ኀጢአት ከሰው ሁለንተናዊ ማንነት ጋር እንደ ድርና ማግ አብሮ ተሰናስሏል። በዚህ መልኩ የክርስትና መልእክት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አንድምታዎች (implications) አሉት።
በዚሁ መሠረት ምድራዊው ኑሮአችን፣ ከአገራችን ሕይወት፣ ትግልና ተስፋ ጋር ከቶ ላይነጠል ተጋምዷል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነው ነገር ሌሎችን በሚመለከትበት መጠንና ደረጃ እኛንም በደጉም ሆነ በክፉ ይመለከተናል። ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ባይተዋር ልንሆን አንችልም። የሰላም ወንጌል “የምሥራችነት”፣ ሰውን “በግለሰብነት” ብቻ ሳይሆን “በማኅበራዊነቱም” የሚመለከት ነው። አገርን የሚመሩ መሪዎችን በመምረጥ ሂደት ውስጥ እንደ አማኝም ሆነ እንደ ማኅበረ ክርስቶስም፣ መንፈሳዊ ኀላፊትነትና ግዴታ አለብን። “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን" ስንል፣ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ በምድራችን እንዲሆን እንዲሁም እንደ እርሱ ፈቃድ “ለሕዝብ መልካም ለማድረግ” የሚተጉ መሪዎችን ለማግኘት መጸለይን ያካትታል። በትውልዳችን ላይ ሊኖረን የሚገባው አንዱ የጽድቅ ተጽእኖ ፈጣሪነት መገለጫ መንገድ፣ መንግሥትን በመምረጥ ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ እንደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደ-ራሴነት ያለን ድርሻና የምንወስነው ውሳኔ ነው። በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ መንግሥታትት ይመጣሉ፤ ይሄዳሉም። በኀጢአት በተለወሰው የዚህ ዓለም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ውስብስብ ውስጥ፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እርሱን በመፍራት ሕዝብን የሚያገለግሉ እንደ-ራሴዎችን መለየት፣ ተአማኒነታቸውን መጠየቅና መመዘን እንዲሁም መምረጥ ትልቅ ኀላፊትና ዐደራ ነው።
1. የክርስቲያናዊ የምርጫ ተሳትፎ ነገረ-መለኮታዊ ፋይዳዎች
1.1) መንግሥት በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ማዕቀፍ ውስጥ የተያዘ ተቋም ነው
“ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” (ሮሜ. 13፥1፤ ቲቶ 3፥1)
እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ ሦስት ተቋማትን ዘርግቷል፤ እነዚህም፣ ቤተሰብ፤ መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን ናቸው። እነዚህ ተቋማት፣ የየራሳቸው የሆነ ገደብ፣ ደንብና ሥርዐት አላቸው። ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥት መጸለይ፤ ሕዝብም ለመንግሥት ሊታዘዝ የሚገባበት ምክንያት ይኸው እውነት ነው። (1ጢሞ. 2÷1-4፤ ቲቶ. 3÷1-2፤ 1ጴጥ. 2÷17)። የአንድ መንግሥት የሥነ ምግባርና የፍትሕ መርሕ በእነዚህ ሦስት አምላክ መር ተቋማት ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። ዜጎቹም መንግሥትን የሚታዘዙበት ምክንያት፣ የመንግሥት ሥልጣን ምንጩ ልዑል እግዚአብሔር በመሆኑ ነው። ይህ መለኮታዊ ሥርዐት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በየትኛውም የመንግሥት ሥርዐት ውስጥ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን፣ ልታስተውል የሚገባት መሠረታዊው ጒዳይ፣ ዐቢይ ተጠሪነቷ የነገሥታት ንጉሥ ለሆነው ለክርስቶስ ኢየሱስ ነው። በዚህ ምድር ላይ አምላክ ቤተ ክርስቲያንን የራሱ “እንደ-ራሴ” አድርጎ በመንግሥታት መካከል አስቀምጧታል። ከዚህ አንጻር፣ “በሥልጣን ላሉት ሹማምንት መገዛት” የሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ፣ የቤተ ክርስቲያንን ማንነት፣ ተጠሪነት እንዲሁም “የክርስቶስ እንደ-ራሴነት” ከግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባዋል።
1.2) የየትኛውም መንግሥት የሥልጣንና ገዢነት ምንጭ እግዚአብሔር ነው
ሥልጣኑን ፍጹምና መለኮታዊ በማድረግ፣ በፍትሕ የለሽነት የታወረው ጲላጦስ፣ “አታናግረኝምን? ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን?” በማለት የጌታን ሥልጣን ሲዳፈር ኢየሱስም፣ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ሥልጣን ባልኖረህ ነበር” (ዮሐ. 19፥11) በማለት የሰጠው መልስ፣ የመንግሥት ሥልጣን አንጻራዊ መሆኑን፣ በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ማዕቀፍ ውስጥ ያለና በልጓም የተገደበ መሆኑንም በግልጽ ያሳየናል። ይህም ዘላለማዊና ፍጹም እውነት የክርስቲያን ሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ አቋም መሠረት ነው፣ “መንግሥት የእግዚአብሔር ናትና፤ ሕዝቦችንም የሚገዛ እርሱ ነው” (መዝ. 22፥28)። ራሳቸው “እንደ አምላክ” ለሚቈጥሩት የሮም መንግሥታት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምድር ነገሥታት ገዥ መሆኑን ሐዋርያው ዮሐንስ አውጇል (ራእ. 1፥4)። እርሱ በኖረበት አስጨናቂ የሮም አገዛዝ ሥርዐት ውስጥ፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው፤ የነገሥታትም ንጉሥ ነው!” ብሎ መመስከር በሞት የሚያስቀጣ ነበር። ይህም የሚያሳየን፣ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ረገድ የነበራት መረዳት፣ የመንግሥታት ሥልጣን የውክልና እንጂ ፍጹም ያለመሆኑን ነው።
1.3) መንግሥት “ለመልካም ነገር የሕዝብ አገልጋይ” ነው (ሮሜ. 13፥4)
ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን፣ የየትኛውም ዐይነት መንግሥት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የአስተዳደር መርሕ፣ አወቃቀርና ተኣማኒነት ልትለካ የሚገባት በዚህ እውነት ላይ ተመስርታ ነው። መንግሥታት ዕውቅና ሰጡም አልሰጡም፣ ለመልካም አስተዳዳር የእግዚአብሔር አገልጋዮች ብቻ ሳይሆኑ፣ የሥልጣናቸውም ምንጭ ራሱ ሉዑል እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ የአገር መሪዎች የሥልጣን ሁሉ ባለቤት የሆነውን፣ እግዚአብሔርን በመፍራት በፍትሕ፣ ለሕዝብ መልካሙን በማሰብና በማድረግ፣ በጥበብና በማስተዋል እንዲያስተዳድሩ ቤተ ክርስቲያን የመማለድ፣ የመምከርና ተጠያቂ የማድረግ ኀላፊትነት አለባት። መቼም ቢሆን ፈሪሓ እግዚአብሔር ያለው በጽድቅ፣ በፍትሕና በምሕረት ላይ የተመሠረተ አመራር ለብሔራዊ አንድነትም ሆነ ለጋራ ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን ማሳሰብ ያስፈልጋል። የአገራችንም መንግሥት የመልካም አስተዳደር መሠረታዊ ዕሴት ዘብ መሆን ይገባዋል። በተለይም የድኾችንና ከዕውቀት ማጣት የተነሣ በደል የሚፈጸምባቸውን ዜጐች መብት ማስከበር ይጠበቅበታል። ከአገሪቱና እንዲሁም ከዓለም ዕድገትና ብልጽግና ክልል መስመር ውጭ ያሉ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል (ኤር. 21፥12፤ ያዕ. 1፥27)።
1.4) የመንግሥት ተአማኒነት መለኪያው የእግዚአሔር ጽድቅ ነው
መንግሥት የእግዚአብሔር የጽድቅ፣ የፍትሕ፣ የፍርድና የምሕረት አገዛዝ አስፈጻሚ ነው። የአገዛዙ ተኣማኒነት መለኪያው ይኸው እውነት ነው።
“ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፤ ገዦችም ትክክል የሆነውን ሕግ ይደነግጋሉ፤ መሳፍንት በእኔ ይገዛሉ፤ በምድር ላይ የሚገዙ መኳንንትም ሁሉ በእኔ ያስተዳድራሉ” (ምሳ. 8፥15-16)፤ “እግዚአብሔር ለዘላለም በዙፋኑ ላይ ነው፤ ዓለምንም በጽድቅ ይዳኛል፤ ሕዝቦችንም በፍትሕ ይገዛል” (መዝ. 9፥7-8)።
ለአመራር ቀውስ እግዚአብሔር በመፍትሔነት ለሕዝቡ በስጦታነት የሚሰጠው እንደ ልቡና እንደ አሳቡ የሚያገለግሉ መሪዎችን ነው። በኀጢአት ቃል ኪዳናቸውን በማፍረሳቸው ምክንያት ወደ ባቢሎን በግዞት ከመወሰዳቸው በፊት እግዚአብሔር ለሕዝቡ አስቀድሞ የገባላቸው የተስፋ ቃል፣ “እንደ ልቤም (የሆኑ) በግ ጠባቂዎችን (እረኞች) እሰጣችኋለሁ፥ በዕውቀትና በማስተዋልም ይጠብቁአችኋል” የሚል ነበር (ኤር. 3÷15)። ስለዚህ መሪዎች ስጦታ ናቸው፤ የአመራራቸው ስኬት ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት እንደሚኖሩት የጽድቅ ኑሮና ፍጹም መሰጠት ይወሰናል።
እግዚአብሔር የሀልዎቱ መተላለፊያ ያደረጋቸው መሪዎች በረከት ናችው። በአገራችን አሁን ላለውም ሆነ ለመጭው ትውልድ የሚያስቡ፣ በየመስኩ ተጨማሪ ብዙ አገልጋይ መሪዎች ያስፈልጓታል። ለራሳቸው ግለኛ አጀንዳ የማይኖሩ፤ ለገዛ ወገኖቻቸው ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለመላው ሕዝብ፣ በተለይም ለድኾች መብትና ጥቅም፣ እንዲሁም ለሚልቀው አገራዊና ሁለንተናዊ ፈውስ የሚጋደሉ መሪዎች በየፈርጁ ያስፈልጓታል። እውነት፣ ጽድቅ፣ ፍትሕና ምሕረት የወንበራቸው መሠረት የሆነ መሪዎች፣ ሕግ አውጭና አስከባሪዎች፣ ዳኞች፣ ኀይላትና ሥልጣናት፣ ወታደሮች፣ አሠሪዎች፣ ባለሙያዎች፣ ባለ ሐብቶች፣ ነጋዴዎች ወዘተ . . . ያስፈልጓታል። ከእነርሱ የተሻሉ መሪዎች ማፍራት ጥማታቸውና ትጋታቸው የሆነ፤ በተሰጣቸው ዘመን ትውልዱንና እግዚአብሔርን ካገለገሉ በኋላ፣ የተሰጣቸውን ኀላፊነት፣ በሕዝብ ለሚመረጡና ለዐደራ የሚበቁ መሪዎች በሰላምና በክብር ለማስረከብ አፍቃሬ ሥልጣን ወይም ወገንተኝነት እንቅፋት የማይሆንባቸው ፈርጀ ብዙ መሪዎች ያስፈልጉናል።
1.5.) የመንግሥት ሥልጣን ምንጭ እግዚአብሔር በመሆኑ፣ ለእርሱ ተጠያቂነት አለበት
“ፍትሕ የጎደለውን ሕግ ለሚያወጡ፣ ጭቈና የሞላበትን ሥርዐት ለሚደነግጉ ወዮላቸው! የድኾችን መብት ለሚገፉ፣ የተጨቈነውን ሕዝቤን ፍትሕ ለሚያዛቡ፣ መበለቶችን ለሚበዘብዙ፣ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለሚመዘብሩ ወዮላቸው!” (ኢሳ. 10፥1-2)።
እግዚአብሔር ለመንግሥት ሥልጣን የሰጠው፣ ሕዝብን ከፍርደ ገምድል፣ ፍትሕ የለሽ፣ ጨቋኝና ንጹሕ ደም አፍሳሽ ከሆነ፣ እንዲሁም ድኾችንና የራሳቸውን መብት የማስከበር ዐቅም የሌላቸውን ዜጐች ከሚጋፋ ክፉ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ሥርዐት ለመጠበቅ ነው። ቅዱስ ቃሉም በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፣ “ገዦች ክፉ ለሚሠሩ እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትፈልጋለህን? እንግዲያስ መልካሙን አድርግ፤ እርሱም ያመሰግንሃል፤ እርሱ ለአንተ መልካሙን ለማድረግ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ነገር ግን ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ምክንያቱም ሰይፉን በከንቱ አልታጠቀም፤ ክፉ የሚያደርገውን ለመቅጣት የቊጣ መሣሪያ የሆነ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው። ስለዚህም ቅጣትን በመፍራት ብቻ ሳይሆን፣ ለኅሊና ሲባል ለባለ ሥልጣናት መገዛት ተገቢ ነው” (ሮሜ. 13፥3-5)። “ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት፣ በጎ አድራጊዎችን ለማመስገን እርሱ ለሾማቸው ገዦች ታዘዙ” (1ጴጥ. 2፥14)። መልካሙን ለማድረግና መልካም አድራጊዎችን ለማመስገን፣ በአንጻሩ ደግሞ ክፉን ለመቅጣት መንግሥት ከእግዚአብሔር የዐደራ ኀይል ተሰጥቶታል። ፍትሕ ሲጓደል፣ የፍርድ ሚዛን ሲዛነፍ፣ የአስተዳደር በደል ሲደርስ፣ ሚዛናዊና ተኣማኒነት ያለው የድምፅ ውክልና ዕጦት ሲኖር መንግሥት የእግዚአብሔር የፍርድ ድምፅ ሊሆን ይገባዋል። ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ የሚያሰማውን የፍትሕ ጩኸት፣ የማዳመጥ ኀላፊነቱ፣ “እርሱ [መንግሥት] ለአንተ መልካሙን ለማድረግ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና” (ሮሜ. 13፥4) በሚለው አምላካዊ ዐደራ ማዕቀፍ ውስጥ የተያዘ ነው። የመንግሥት ተጠያቂነት፣ በዚሁ የፍትሕ፣ የሰላምና የጽድቅ “አገልጋይነት” ድንበር ውስጥ የተካተት ነው። መንግሥት “መልካም አገልጋይ” በመሆን ፈንታ፣ አምባገነን፣ ክፉ፣ አስጨናቂና በዳይ ሲሆን፣ በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ወድቋል!
1.6.) ኅሊና - የአማኝ የሞራልና ሥነ ምግባር ውሳኔዎች ዳኛ
“ለኅሊና ሲባል ለባለ ሥልጣናት መገዛት ተገቢ ነው” (ሮሜ. 13፥3-5)። ይህም ማለት፣ የማንኛውም መንግሥት አገዛዝ፣ ዐዋጆችና አፈጻጸሞች፣ በእግዚአብሔር ሉዐላዊ አገዛዝ ገደብ የተበጀላቸው ከሆነ፣ ከገደባቸው ሲያልፉ አማኝ፣ መታዘዝ ያለበት ለኅሊናው ነው፤ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል”! (የሐዋ. 5፥29)። (የቄስ ጉዲና ቱምሳ ዝክር ይህን ያስታውሰናል!) ከፍተኛውና የላቀው ሥነ ምግባር አምላካዊ እንጂ፣ ምድራዊ አይደለም። የግብፅ የባርነት አገዛዝ ያወጣውን ወንድ ሕፃናትን የመግደል ዐዋጅ፣ በሕይወታቸው በመወራረድ ያልታዘዙት ዐዋላጆች ምክንያት ይኸው የኅሊና የበላይነት ነበር፣ “አዋላጆቹ ግን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ስለ ፈሩ የግብፅ ንጉሥ ያዘዛቸውን አልፈጸሙም፤ ወንዶቹንም ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ተዉአቸው” (ዘፀ. 1፥17)። የአስተዳደራዊና የኢኮኖሚያዊ ኢ-ፍትሐዊነትን፣ ከጽድቅ ሥራ የተለየ ምውት ሃይማኖተኝነትንና ሥነ ምግባራዊ ቀውስን አስመልክቶ፣ መጥምቁ ዮሐንስ ለሕዝብ፣ ለፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን፣ ለቀረጥ ሰብሳቢዎች፣ ለወታደሮችና ለገዢዎች በቀጥታ ይናገር ነበር። ይህን እውነት የሕይወት ዋጋ ከፍሎበታል (ሉቃ. 3፥7-19)። የትኛውም መንግሥት፣ የዜጎቹ መልካም እረኛ የመሆን ዐደራ አለበት።
በድጋሚ - እግዚአብሔር መንግሥታትን የሚያስቀምጠው፣ የእርሱ የጽድቅ፣ የፍትሕና የምሕረት አገዛዝ አስፈጻሚ እንዲሆኑ ነው። የአገዛዛቸው ፍትሓዊ ተኣማኒነት ልኬቱ ይኸው እውነት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ተልእኮው፣ ኀይላት ጋር አጋጭቶታል። እንዲያውም፣ የከሰሱት፣ የፈረዱበትና በመጨረሻም እንደ ወንጀለኛ የሰቀሉት የአይሁድ ሃይማኖትና የሮም መንግሥት ኀይላት በጣምራ በመሆን ነበር፤
2. የምርጫ 2013 ዐውድ በክርስቲያናዊ ፋይዳዎች
በፖለቲካ ምርጫ ሂደት ውስጥ እንዲሁም ከምርጫም በኋላ፣ የአንድ አማኝ ዕይታ በቤተክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ሊኖረው በሚገባው አጠቃላይ የመስተጋብር ማዕቀፍ ውስጥ የተያዘ ሊሆን ይገባዋል። ከገዢውም ሆነ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የምንጠብቃቸውን ፖሊሲዎች ስንመዝን እንዲሁም ያዋጣናል የሚለውን መንግሥት ስንመረጥ፣ ይህ ጽሑፍ መነሻ መርሕ እንደሚሰጥ ተስፋ አደርጋለሁ።
የየትኛውም ፓርቲ እውነተኛ ልማትና ዕድገት መለኪያው፣ ለሰው በሚስጠው ዋጋ ይለካል። ረጅምና አድካሚ የዲሞክራሲ ግንባታ መንገድ ፊታችን አለ። አሁን እንደ አገር ካለንበት አጣብቂኝ፣ ወደ ተረጋገጠ የጋራ ሰላምና ዕድገት ሊያወጣን የሚችል ማንም ሊረዳው የሚችል ግልጽና ተግባራዊ ራእይ ያስፈልጋል። በተለይም ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አራት ዐቢይ ዘርፎች ዙሪያ፦
2.1. በፖለቲካ ዘርፍ -
2.1.1. የሰው የሕይወት ዋጋ፣ ክብሩነትና እኩልነት። የእግዚአብሔር ፈጣሪነትና የሰው አምሳለ-እግዚአብሔር ተሸካሚነት፣ የሰው ሕይወት ዋጋ፣ የእኩልነት፣ የሰብአዊ ክብሩ መሠረት፣ የፍጥረት በረከት ተካፋይነት ነባራዊ መሠረት ነው (ዘፍ. 1፥ 26-27)። ። ክርስቲያኖች የፓለቲካ ፓርቲዎችን ዕሴት የሚያዩበት ዕይታ፣ በዚህ አይገረሰሴና ዘላለማዊ እውነት የተቃኘ ሊሆን ይገባዋል። ከማዕከላዊ መግሥት አንስቶ እሰከ አንድ ግለሰብ ድረስ ያለው መዋቅራዊ የግንኙነት ሰንሰለት፣ ይህን እውነት ያረጋገጠ መሆኑን መፈተሽ ያስፈልጋል።
2.1.2 ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት። "ምን አይነት ፈዴራሊዝም?" የሚለው ትልቅ የወቅቱ ጥያቄ ምላሽ ያሻዋል። ተከፋፍሎ ያደገ ሕዝብ የለም። የብሔር ማንነት ሳይኰሰምን አገራዊ አንድነት ሊጠናከር ይገባዋል፤ አንዱ በሌላው ኪሳራ ላይ መገንባት የለበትም። ተከፋፍሎ በሰላም የኖረና ያደገ ሕዝብ እንደሌለ ታሪክ ምስክር ነው። በክልላዊ ራስ-ገዝነትና በማዕከላዊነት መካከል፣ ተመጋጋቢ፣ ጤናማ እንዲሁም አንዱ ለሌላው ማበብ አስተዋጽዖ የሚያደርገበት ትስስር መፍጠር ያልተፈታ የዘመናት ጥያቄ ነው። የብሔር ልዩነቶች፣ ልክ እንደ ጥልፍ የአገራችን አንድነት የተሠራበት ጌጦች እንጂ የማግለያ አጥር ሊሆኑ አይገባም። ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን፣ “እንደ አሀዳዊነትና እንደ ጠቅላይነት” በመስበክ፣ ለክፍፍልና ለዘመነ-መሳፍንታዊነት እያንደረደረን ካለው መወጋገድ በጋራ ለመውጣት መወሰን አለብን። በዚህ ረገድ ፓርቲዎች ያላቸው ራእይና የመፍትሔ ሀሳብ ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። እንዳንለያይ ተደርገን በቋንቋ፣ በባሕል፣ በመዋለድና በጋራ ታሪክ የተገመድንና ከብዙ ብሔሮች የተሠራን አንድ ሕዝብ ነንና!
2.1.3 የሕግ የበላይነት፣ የሰላምና የፍትሕ ጥያቄ። ዜጐች በአገሪቱ የትኛውም ክልል ለመኖር፣ የምድሪቱም በረከት ትሩፋት ተካፋይ እንዲሆኑ የሚያስችል የሕግ የበላይነትንና የሰላምን ዋስትና ያረጋገጠ ራእይ ያስፈልጋል። የፍትሕ ጥያቄ ክርስቲያናዊ ምላሽ እሴታዊ መሠረቱ፣ አምላካችን ለተበደሉ፤ ለተጨቆኑና ለድኾች ጩኸት የሚራራ አምላክ መሆኑ ነው፤ “መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን እሹ፣ የተገፉትን አጽናኑ፤ አባት ለሌላቸው ቁሙላቸው፤ ለመበለቶችም ተሟገቱ” (ኢሳ. 1፥ 17)። እውነተኛ አምልኮ ከፍትሕ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው (ያዕ. 1፥27; 2፥15-17፤ ሚክ. 6፥8፤ 1ዮሐ. 3፥17)። ብሔር ተኮር በሆነ አረመኔአዊ ጭከና፣ ንጹሓን በሚገደገሉባትና በሚፈናቀሉባት አገራችን፣ ጸጥታን፣ ደህንነትን፣ ሰላምን፣ የአገርን አንድነትና ድንበር ማስከበር የሚችል ዐቅም ያለው መንግሥት ያስፈልግናል። ይህን በተመለከተ፣ መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያላቸው ግልጽና ተግባራዊ ዕቅድ ምንድነው?
2.1.4. ብሔራዊ ይቅርታና ዕርቅ ራእይና ዝግጅት። በብሔርተኛ ጽንፈኝነት እየሻከረ ያለው የክልሎች ግንኙነት፣ በሕዝቦች መካከል ዕርቅና ሰላም በማውረድ አስቸኳይ መፍትሔ ያስፈልገዋል። በፍትሕ፣ በይቅር ባይነት፣ በዕርቅና በፈውስ ላይ ወደ ተመሠረተ አገራዊ መግባባት የሚወስደን ራእይ የዚህ ምርጫ ዐቢይ አጀንዳ ሊሆን ይገባዋል።
2.1.5. ሰላም-መርና ጸረ ዐመፅ ፖለቲካዊ የራስ ግንዛቤ። የትኛውም ፓርቲ ለዚህ መርሕ በጎ ፈቃደኝነት ተገዢ መሆንኑ ሕዝብን ለማገልገል ያለው ተአማኒነት አንዱ ወሳኝ መለኪያ ነው። ፓርቲዎች ለፍትሐዊና ለሰላማዊ እንዲሁም ለሕዝብ ድምፅ የመጨረሻ የበላይነት ተገዢ መሆናቸውን መጥየቅ ያስፈልጋል። አሸናፊው ፓርቲ ለድሉ፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ የሕዝብን ልብ ከማግኘቱ የተነሣ እንደሆነ በትሕትና በመቁጠር፣ የገባውን ቃልና የሰጠውን ተስፋ ለመፈጸም ያለው “የሕዝብ አገልጋይነት” መንፈስ መመዘን ያስፈልጋል። የተሸነፉትን ፓርቲዎች ደግሞ እንደ ተቀናቃኝና ክፉ ባላንጣ ሳይሆን፣ እነርሱንም እንደ ሕዝብ ተመራጭ አገልጋዪች አክብሮ ለመቀበል ሰፊ ትከሻ ያለው ሊሆን ይገባል። ተሸናፊ ፓርቲዎች፣ ወደ ዐመፅ የማይሄዱና፣ የሕዝብን የምርጫ ፈቃድ በጸጋ የሚቀበሉ መሆናቸውና በሰላማዊ መንገድ ለሌላ ምርጫ በተስፋ ለመሥራት ያላቸው ተነሳሽነት እጅግ አስፈላጊ ነው። ቅቡልነትንና ተኣማኒነትን ገንዘቡ ያደረገ የፖለቲካ ሥርዐት መመሥረት የሚቻለው ሕዝብ ልቡን በነጻ ምርጫ፣ አምላክ ደግሞ ሞገሡን ሲሰጥ ብቻ ነው። መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህን ሊገነዘቡ ይገባል። መጪው ምርጫ ፈሪሓ-እግዚአብሔር የሚገዛው፣ ግልጽ፣ ፍትሕዊ፣ ሰላማዊ እና የሕዝብን የድምፅ የበላይነት ያረጋገጠ ቢሆን፣ ለአገራችን ትልቅ ፈውስና ተስፋ ይሆናል!
2.2. በምጣኔ ሀብት ዘርፍ -
2.2.1. ድኻን ወጋኝ የትምህርት፣ የጤና፣ የፍትህ፣ የንግድ፣ የተፈጥሮ እንክብካቤ፣ ለሕጻናት፣ ለሴቶች፣ ለአረጋዊያ እንዲሁም በተፈጥሮም ሆነ በአደጋ የአካል ውሱንነት ላለባቸው አሳቢ። የኑሮ ውድነትን የሚስወግድ፤ በውጭ ዕርዳታ ተደጋፊነትን እንዲሁም የብድር ዕዳን ቀና አገር አበልጻጊ የኢኮኖሚ መርሕ።
2.2.2. ሙስና ጸያፍና አስወጋጅ፣ - ነጋዴዎችና ባለሀብቶች፣ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሁም በጽድቅ እንዲበለጸጉ፣ ለአገር በረከት መሆን የሚያስችላቸው ዐቅም የሚያሳድግ ፖሊሲ።
2.2.3. ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን መሠረት ያደረገ ራእይ
2.2.4. የሥራ ሥነ-ምግባርዊነት አጎልባችነት - የሕዝብን ሥራ ወደድና ሕግ አክባሪ ባሕል የሚያሳድግ
2.2.5. በውጭ ዕርዳታ ተድጋፊነት እንዲሁም የብድር ዕዳን ቀናሽ
2.3. በየውጭ ግንኙነት ዘርፍ - የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብርና ከጐርቤት እንዲሁም ከዓለም ዐቀፍ ማኅብረሰብ ጋር በመከባበርና ፍትሕ ባለው የጋራ ጥቅም ሊያኖራት የሚያስችል የውጭ ግንኙነት።
2.4. የማኅበረሰብ ሞራልና ሥነ-ምግባር ፋይዳዎች ዘርፍ -
ሰው ሞራላዊ ፍጡር መሆኑን ታሳቢ በማድረግ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ከተወጠረችበት ውጥረት ሊያወጣት የሚያስችል ኅብረተሰባዊ ሞራልና የሥነ-ምግባር ሥር ነቀል ተሐድሶ ያስፈልገናል። ለኀሊናው ዳኝነት ያልተሸነፈን ዐመፀኛ ልብ ሕግ ሊገዛው የሚችለው እጅግ ውሱንነት ባለው መልክ ብቻ ነው። ዲሞክራሲያዊ ብስለት፣ ኢኮኖሚያዊ ፍሬያማነትና የዜጐች ደስታ፣ ከማኅበረሰብ የሞራልና የሥነ-ምግባር ብስለት ጋር ቀጥጠኛ ግንኙነት አለው። ደቦ ፍርድ፣ አግላይነት፣ ተጠራጣሪነት፣ ወገንተኝነት፣ ንፉግነት፤ የተደራጀ ዘረፋ፣ ውርጃ፣ ግብረሰዶማዊነት፣ ወሲባዊ ጥቃት (በሕጻናት ሳይቀር) የፍትሕ-ጥሰት፣ የፍርድ መዛባት፣ ጉቦና ሙስና ለጐረቤት ያለማሰብና ጭካኔ፣ ሃይማኖት/ብሔርን መሠረት ያደረገ ስደት፣ እንደ አገር ያለንበትን የሞራል ዝቅጠት ያሳያሉ። የዲሞክራሲ ባሕል ዐቅም ግንባታ፣ ከአስተሰሰብና ሥነ-ምግባር ግንባታ ጋር ሊለያይ አይችልም። የአስተሳሰብ ለውጥ፣ የልብ ለውጥ ያመጣል፣ የልብ ለውጥ የድርጊት ለውጥ ያመጣል። የፓርቲዎች ሞራልና ሥነ-ምግባር ራእይ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ንጽረተ ዓለም (Biblical Worldview) ምልከታ መሠረት ሊፈተሽ ይገባል።
ማጠቃለያ
እግዚአብሔር ሦስት ተቋማትን መሥርቷል - ቤተ ሰብ፣ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት። እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ የግዛት ክልል አላቸው። አንዱ በሌላው ላይም አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ አለው። በዚህ አጠቃላይ ዐውድ፣ መጸሐፍ ቅዱሳዊ ንጽረት-ዓለምን ግምት ውስጥ ያስገባ የምርጫ ውሳኔ ማድረግ፣ በእግዚአብሔር ፊት የሚደረግ የተቀደሰ ግላዊ ኀላፊነት ነው። መመረጥም ሆነ መምረጥ፣ የአገርንና የትውልድ አቅጣጫ ይወስናል። ከዚህ አንጻር፣ የእያንዳንዱ አትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታና ኀላፊነት ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ድምፅ ወሳኝ አስተዋጽዖ አለው። ያለመምረጥ፤ ባልመረጥነው አካል ለመገዛት መወሰን ነው። ይህ የትውልድን አቅጣጫ የመወሰን ግድ የለሽነት ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትም አለበት። ምርጫ ክርስቲያናዊ የጽድቅ ተጽእኖ ማምጫ ወሳኝ መንገድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
ምርጫ፦ ጐረቤትን እንደራስ ከመውደድ ይጀምራል። የጎረቤታችንን፣ የኅሊናና የማሰብ ነጻነት፣ ሐሳብን የመግለጥና ያዋጣል የሚለውን ፓርቲ የመምረጥ መብቱን ማክበር ይጨምራል። የፓለቲካዊ ዕይታዎች ልዮነቶች አንጻራዊነት በማክበር፤ በክርስቶስ ያለንን ገዢ ማንነትና አንድነት ከማናጋት መጠንቀቅ ይኖርብናል። እንደ ክርስቲያንም እንደ ኢትዮጵያዊም ፍትሕና ሰላም ያለው ምርጫ እንዲደረግ መጸለይ፤ የሰላም መልክእክተኛ በመሆን፣ የሕዝብ የመጨረሻ ወሳኝነት እንዲከበር የራስን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠይቃል። እንደ ግለሰብ አማኝ፣ የማንፈልገው ሰው ቢመረጥ እንኳን፣ ሕግን በመከተል ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በሕዝብ እስከ ተመረጠ ድረስ፣ ማክበር ይኖርብናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ልናሳድገው የሚገባው የዲሞክራሲ ባሕል፣ ሕዝብን የማያገለግል መንግሥትንም ሆነ ፓርላማ፣ በጅምላ ጥላቻና በዐመፅ ኀይል ሳይሆን፣ በምርጫ ማስወገድን ነው።
የምርጫችን ዕሴት መሠረቱ፣ ብስለትና አመክንዮአዊነት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሊሆን ይገባዋል። ጭፍን ከሆነ ጐሳዊ ወይም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ራሳችንን መጠበቅ አለብን። ኀላፊነት ባለው መልኩ የማኅበራዊ መገናኛዎች መጠቀም ይኖርብናል። ሕዝብን ከሚያጣሉ የሐሰት መረጃዎች እንዲሁም፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ (በስሜት ተገፋፊነት)፣ የክፋት ስርጭት መንገድ ልንሆን አይገባም። እግዚአብሔር ይህን ይጸየፋል። በአገርና ከአገር ውጭ ያለን ኢትዮጵያውያን በሙሉ፣ ከምንጊዜውም በላይ ለገዛ ኀሊናችን ስንል የሰላምና የእውነት እንደራሴዎች የመሆን ዐደራ ወድቆብናል። ከጥቂት ጽንፈኞች ዕኩይ ተግባር የተነሣ እርስ በእርስ በጅምላ ከመፈራረጅና ከመወጋገድ ፈተና በመጠበቅ፣ በአንድ ላይ ለሰላም፣ ለእውነትና ለጽድቅ ልንቆም ይገባናል። በየትኛውም መልኩ ከዐመፅ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጋር ባለመተባበር፣ የምርጫ ሕጐች እንዲከበሩ እንዲሁም ከምርጫ ውጤት ጋር የሚነሱ ውዝግቦች፣ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እንዲፈቱ የበኩላችንን አስተዋጻዖ ለማድረግ ከወዲሁ የቆረጥ ልብ ያስፈልገናል።
እንጸልይ፣ እንመዝን፣ እንምረጥ፣ የምርጫውን ፍትሐዊ ሂደት በቅርብ እንከታተል፤ ውጤትን በደስታና በጸጋ እንቀበል። ዲሞክራሲ ፍጹምና እንከን የለሽ ደረጃ አይደለም፤ ይልቁንም ፍጹምናው በየጊዜውና በየትውልዱ የሚያድግ እንጂ! ትልቁና ዋናው የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የሰውን ልብ በወንጌል መማረክ ነው፤ ወንጌል የለወጠው ልብ ለአገር ሰላምና ዕድገት በረከት ነው!
©ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ ኢትዮጵያ። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።