መጣጥፎች

ኮቪድ 19፡ ዕድል ወይስ ተግዳሮት

በክብሩ ታደሰ

May 1, 2020

ዕድል ሁሉ ተግዳሮትን፤ ተግዳሮትም ሁሉ ዕድልን ያረገዙ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው!!!

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለማችን ሁሉንም አውታሮች ተቆጣጥርሮ ብቸኛ አጀንዳ ከሆነ ቀናትን አልፎ ወራት ማስቆጠሩ እውን ሆኗል።

የቤተክርስቲያን የአምልኮ ስብሰባዎችን ለማቆም መወሰንም፤ አመለካከቶችን በሁለት ከፍሎ ሲያነታርክ ማየቴና ትኩረቴን መሳቡ ለጽሁፌ መነሻ ነው። ወረርሽኙ ለህይወት የሚያሰጋ ተግዳሮት ሆኖ እንደመምጣቱ ምላሹ በስሜት የሚሰጥ ሊሆን አይችልም።

መንግስት ሳይንሱን ተከትሎ መሰብሰብንና ንክኪን በተቻለ መጠን ማስወገድ አልያም መቀነስ ይገባል የሚል አቅጣጫ ሲያስቀምጥ ብዙዎቹ መሪዎቻችንም የእሁድን አምልኮ ጨምሮ ስብሰባዎችን መሰረዙን ተገቢ እርምጃ አድርገው ወስደውታል። ድፍረትና እምነት፤ እውቀትና ስሜት፤ ፍላጎትና አቅም፤ መሪነትና ተከታይነት ድንበሩ በውል በማይስተዋልበት ማህበረሰብ ውስጥ ቆም ብሎ ጉዳዩን በማጤን ተገቢ ያሉትን እርምጃ ለመውሰድ የወሰኑትን መሪዎች ሳላደንቅ አላልፍም። መሪነት ውሳኔ ሰጭነትን የሚጠይቅ ስራ ነውና።

ስለመሪዎች ይህን ካልኩ የመሪዎችን ውሳኔ በመቃወም መሪ ለመሆን ከሚሞክሩት ይልቅ ገብቷቸውም ይሁን ሳይገባቸው ለመሪዎቻቸው የታዘዙትን አማኞች ትህትና አለማድነቅም ተገቢ አይሆንም። መንፈሳዊነት የሚለካው በገባንም ባልገባንም ከመሪዎች ጋር ትከሻ ለትከሻ በመለካካት ሳይሆን በመታዘዝና ያልገባንን በትህትና በመጠየቅ ነው የሚል ጽኑ አቋም አልኝ። መጽሐፍ ቅዱስ እንኳንስ መሪዬን ባለንጀራዬ ከኔ እንዲሻል እቆጥር ዘንድ አይደል ጥሪው። ፊሊ. 2፡3 “ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትህትና ቁጠሩ እንጂ፤ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ።” መሪዬ ያልገባኝ ገብቶት፤ ያልታየኝ ታይቶት ይሆናልና እየታዘዝኩ ዕድል ሳገኝ ልጠይቀው ማለት ከብዙ ስህተት ይጠብቃል።

ወረርሽኙ ምንጩ ምንድነው?

የእግዚአብሔር ቁጣ? ሰዎች ሌላውን ለማጥፋት የፈጠሩት ክፋት/ተንኮል? የተወጠረውን፤ ሁሉን ተቆጣጥሪያለሁ የሚለውን የሰውን ልብ ማስተንፍፈሻ? የጌታ ዳግም ምጻት በመቃረቡ የግድ ሊሆኑ ከሚገባቸ ምልክቶች መካከል አንዱ ይሆን? ሌላም ሌላም መላ ምቶችን ማስቀመጥ እንችላለን። በአሁኑ ሰዓት ግን አንገብጋቢው ጥያቄ በምን መልኩ እናስተናግደው? የሚል ይመስለኛል።ከላይ ላነሳነው ጥያቄ ምንም ቢሆን መልሱ፤ ጌታ ተቆጥቶንም ከሆነ ማለቴ ነው፤ ወደ የቤታችሁ ግቡ! ያለን አይመስላችሁም?

“ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤. . . ” መዝ. 46፡10

የዘመኑ ፍላጎት/demand/ በየትኛውም መስክ ላይ ሆነን ዕረፍትን እንዳናስብ ብሎም እንደስንፍና እንድንቆጥር ያደገን ከመሆኑም ባሻገር፤ ያለውን ጥያቄ ለመመለስ ሲባል 24/7(በቀን 24 ሰዓታት በሳምንት 7ቀናት) ለመሮጥ ከቡናና ኮካ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ አነቃቂና ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም የተለመደ ሆኗል። አማኞችና አገልጋዮችም ሆነን በክርስቶስና በፈጸመው ስራ ላይ በማረፍ ሳይሆን በመሮጥ ብዛት በምንደርስበት ስኬት ጌታን ለማስደሰት መወራጨቱን ስራዬ ብለን ተያይዘነዋል። “ቁሙ! የሚሆነውንም የእግዚአብሄርን መድኃኒት እዩ!. . .” 2ዜና 2፡17 የሚለው ቃሉ ሩጥ! አቅምህን፥ እምቅ እሎታህን፤ የአስትሳሰብ ምጥቀትህን፤ አይበግሬነትህን፤ ከሌሎች መሻልህን፤ ማድረግ የምትችለውን ታምራት እይ(አሳይ)! በሚል የተተካ ይመስላል።

ማን ያውቃል?

ከዚህ ውድቀታችን ሊያነሳን፡

በጩኸት ብዛት ማድመጥ የተሳነንን ድምጹን በጥቂት ዝምታ ውስጥ ሆነን እንድናስተውለው ሊያግዘን

በግርግር መሃል ገብተን ከተረሳሳነው መገኘቱ በጸጥታ ውስጥ ወደምንለማመደው መገለጡ ሊያሻግረን፤

በሩጫ ብዛት ከተጠፋፋነው ራሳችንና ቤተሰባችን ጋር ሊያስታርቀን፤

ከአፀላይነት ወደ ፀላይነት፤ ከተመጋቢነትና አስመጋቢነት ወደ መጋቢነት ሊያሳድገን፤

ስንዴ ከመውቃት ወጥተን ለህዝባችን ነጻ መውጣት ወደምንታገልበት ከፍታ ሊያወጣን፤ በግል ሊያገኘን ፈልጎ አንድ ዕድል ሰጥቶንስ ቢሆንስ?

ዕድላችንን አናባክነው እንጠቀምበት!!!

©ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ ኢትዮጵያ። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።