መጣጥፎች

እናትነት ፡ ባለአደራነት ወይስ ባለእዳነት

ቤተልሔም አበራ

May 11, 2020

 

 

አለም አንድ መንደር ናት ስንባል ሰንብተናል። የሰው ልጆች ከቦታ ቦታ ዝውውር፣ የቴክኖሎጂ ማደግ ፣ የአለም አንድ አይነት ባህልና መረጃ መጋራት ይህን እሙን አድርጎታል ። የዘንድሮው ያልተጠበቀውና ለመቆጣጠር ከሰው ልጆች አቅም በላይ እየሆነ የመጣው የኮሮና ወረርሽኝ  (COVID-19)  ይህንኑ ሀቅ ያረጋግጣል ።

ታዲያ ድሮ  ድሮ  የነጮች የባህል ወረራ አድርገን የቆጠርናቸው ነገሮችም ከዚሁ ጋር ዘው ብለው ገብተው የዕለት ተዕለት የህይወታችን መገለጫ ከሆኑ ሰንበትበት ብለዋል።

የዘንድሮውን የአለም አቀፍ የእናቶች ቀን መታሰቢያ በዓል ስናከብር ለቤተሰባችን አራተኛ የሆነውን ልጃችንን ወልጄ እቤት ባለሁበትና የሙሉ ጊዜ እናትነትን በእጅጉ እያጣጣምኩ ባለሁበት ወቅት መሆኑ ደስታዬን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል ።

አለም አቀፍ የእናቶች መታሰቢያ በዓል ቀን በየአመቱ የሚለያይ ቀን ላይ የሚዉል ቢሆንም ለአጠቃላይ መግቢያባነት በአውሮፓዊያን አቆጣጠር  በሜይ ወር በሁለተኛው እሁድ ይሆናል ። ከስሙም ከታሪኩም እንደምንረዳው ቀኑ እናቶችን ለማወደስ የተሰየመ ነዉ። ምንም እንኳ የእናቶችን ገድልና ዋጋ በአንድ ጀንበር ሂሳብ ማወራረድ ባይቻልም ።

ይህን ቀን አስገራሚ የሚያደርገው ታዲያ የዚህ በአል  ሀሳብ አመንጪ የሆነቸው ሴት ዘ ማዘር ኦፍ ማዘርስ ዴይ Anna Jarvis እራሷ የወለደቻቸውም ሆነ ያሳደገቻቸው ልጆች አለመኖሩና በ 1908 እሷ ራሷ ያልተገኘችበት በአል በተከበረበት ጊዜ የቴሌግራም መልዕክት መላኳ ነዉ።

በሌለው አንፃር ደግሞ ከእርሷ ፍለጎትና ራዕይ ዉጪ በሆነ መልኩ ይህ በአል በአለም አቀፍ ደረጃ ከክሪስማስ Christmas  ቀጥሎ ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበትና ለንግዱ አለም ፍጆታ ላይ የዋለ መሆኑ አስደናቂ ያደርገዋል ።

መጽሐፍ ቅዱስ እናቶችን ለመዘከር የሰየመው ዕለት ባይኖረውም የእናቶች የህይወት ንፅህና ፣ ተግባርና ኑሮ ግን እንዲመሠገን ለሌሎችም አርአያ እንዲሆን ያበረታታል ።  መጽሐፉ የእናትነትን ዋጋ  ከ ቀይ እንቁ፡ ፍቅሯንም ከ አግዚአብሔር ፍቅር ጋር ያወዳድራል።

መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንዳይሉ መጽሐፍ ቅዱሳችን ይች ውዳሴ የሚገባት እናት ምን እንደምትመስልና ምሳሌነቷንም ፍንትው አድርጎ ያሳየናል ።

ሴትነት ዉስጥ እናትነት ፣

እናትነት ዉስጥ ደግሞ ሴትነት

ሚስጥራዊ የተፈጥሮ ስጦታ ናቸው ። 

 

ይሁን እንጂ ሴትነት የእናትነት ታላቅ እህት ናት ። በዚያው ልክ ደግሞ ሴትነትም፡ 

እናትነትም የራሳቸውን ኀላፊነትም ተጠያቂነትም ይዘው ይመጣሉ። በመጽሐፍ ቅዱስም ይሁን በአለማችን ላይ ብዙ ሊዘከሩና አርአያነታችዉ ሊቀሰም የሚገባችዉ፣ታዋቂ ሳይሆኑ አዋቂ የሆኑ፣እናትነት ባለእዳነት ሳይሆን ባላደራነት የሆነላቸዉ የተፈጠሩለትን አላማ በአግባቡ ከዉነዉ ያለፉ በርካታ እናቶች አሉ።

 

 

...የባልዋ ልብ ይታመንበታል፣

ምርኮም አይጎድልበትም።

ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች።...

መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፣

አንቺ  ግን ከሁሉ ትበልጪያለሽ። ምሳሌ 31፡10-31   

ከላይ እንዳስቀመጥኩት መነሻ የእግዚአብሔር ቃል " አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጪያለሽ" የተባለችዉ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ነች። የዚህች ሴት ልዩነቷ ውጫዊ ማንነቷ ሳይሆን እግዚአብሔርን የምትፈራ መሆኗ ነው።  ይህ እግዚአብሔርን መፍራቷ ቀጥተኛ ከሆነዉ ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ሳይሆን ወደ ጎንዮሸም ከሰዉ ሁሉ ጋር ነበር ስኬታማ ያደረጋት። ዛሬ ዛሬ እግዚአብሔርን መፍራት ከህይወታችንና ከኑሮአችን እየጠፋ ስለመጣ ነሮቻችን በሙሉ ብልሸት ያሳያሉ።

 

የወርቃማዉ እናትነት መርሆዎች፦

        1. አትፎካከርም

ተረቱም እንደነገረን የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል። በዚህም ፍርሀቷ ያለፉክክር ቤቷን ለመገንባት ደፋ ቀና ስትል እናያታለን።ሁሉን በስርአት ትመራለች። አሁን ባለንበት አለም ፉክክር ስለበዛና የማያዋጣ፣መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ አስተሳሰብ ዉስጥ ስለገባን ነዉ ቤቶች እየፈረሱ፣ ትዳሮች እየተበተኑ፣ ሕፃናት ያለወላጅ እየቀሩ፣ ያሉት።  ቤት በብልሀት ይገነባልና ሁላችንም እናስብበት። የገባንበት በላደራነት አቛራጭም መዉጫም የለዉም። ርቀትን ጠብቆ ፍጥነትን ገድቦ መብረር ነዉ።

          2. ትጉ ናት

ትጋት መታወቂያዋ፣ ብርታትና ከበሬታ ልብሷ ናቸዉ ። ምንም እንኳን በአጋሮችና በዘመድ ድጋፍ ሀላፊነታችንን ማጋራት የምንችልበት ሁኔታ ዉስጥ ብንሆንም ቤታችን ያለእኛ አስተዳደር ሙሉ አይሆንም። አገልግሎት ከቤት ይጀምራልና በቤትና በዉጭ ሀላፊነተቻችን መካከል ሚዛናዊነት ሊኖር ይገባል። መልካም ስራዎቿና ገድሏ በአደባባይ ያመሠግኗታል። 

        3. የምትመች ረዳት ናት

እንደ ተፈጠረችለት አላማ  ለባሏ የምትመች ረዳት ናት። ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች።  ምርኮም አይጎድልበትም። መልካምነቷ በጊዜ፡ በሁኔታ፡ በማግኘት በማጣት የተገደበ አይደለም። መልካምነቷ በመልካም ግንኙነት ላይ ተመሰረተ ነዉ። የጤናማ ግንኙነት የሚጀምረዉ ደግሞ ከፈጣሪ ጋር ባለ ጤናማ ግንኙነት ነዉ።  የኔና የናንተስ ምን ይመስላል? ወደ ቀደመዉ ወደ ተፈጠርነለት አላም እንመለስ።

        4. ለድሀ ትሰጣለች 

እጅዋን ወደ ድሀ ትዘረጋለች፣ወደ ችግረኛ እጅዋን ትሰዳለች። መልካም እናት ስጦታዋ እንካ በእንካ አይደለም።  በአፀፋዉ የምትጠብቀዉ የለም። አርጌለሁ በሚል ሰበብም የደሀዉን ጉልበት አትበዘብዝም። አሁን ባለንበት ወቅት በጣም አስፈላጊ መልዕክት ነዉ።  እንዴት እየተወጣነዉ ይሆን?  ቃሉ ለድሀ የሚሰጥ ለእግዚአብሔር ያበድራል ይላል።

        5. ዘመኑን የዋጀች ናት።

ይቺ ሴት በኋለኛዉ ዘመን ላይ ትስቃለች ። ዘመኑ አያስፈራትም ይልቁን ለሷ እድል ነዉ። ቀድማ ተዘጋጅታለች። አሰራርና አደራረጉን ታዉቃለች። እኛ ዘመኑን በመዋጀት ረገድ ምን ያህል በሁለንተናችን ተዘጋጅተናል። ይህንን ጊዜ እንዴት እየተጠቀምነዉ ነዉ?

        6. ባለሙያ ናት

በእጀቿ ሙያ የዉስጡንም የዉጪዉንም ታሳልጣለች። ያለዉን የማስተዳደር ብቃት፣ የሌለዉን ፈጥሮ የማቅረብና ከቤቷ አልፎ ለዉጪ ሰዉ የሚበቃ ልግስና በእጇ ጥረት ለሌሎች የምታካፍለዉ ነገር አላት። 

እነዚህና ሌሎች መሰል ተግባሯ ናቸዉ ምስጋናን የለገሷት። ስራዎቿ በሸንጎ፣ ባለቤቷና ልጆቿ በአደባባይ ያመሰገኗት።

እንግዲህ ይህን የእናቶች ቀን መታሰያ ስናከበር መዘንጋት የሌለብን አንድ እዉነት አለ። ይሄዉም የህያዋን ሁሉ እናት የሆነችወን ትዉልድ ሁሉ የረሳት የሐጢያት ምንጭ ተብላ የምትታሰበዉን እናታችንን ሔዋንን።

ዛሬ እኔ ላስታዉሳቸሁ የፈለኩት ዉድቀቷን ሳይሆን የተገባላትን የተስፋ ቃል ነዉ። ሐጢያት በእሷ በኩል ወደ አለም መግባቱን የተመለከተዉ ጌታ መድሐኒትም በእርሷዉ በኩል ለሰዉ ልጆች ሁሉ እንዲመጣ ቃል ገባላት። በአንተና በሴቲቱ መካከል፣በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል።ዘፍጥረት 3:15። ለዚህም ነዉ ማርያም ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅን ስራ አድርጓል ስሙ ቅዱስ ነዉ ያለችዉ። ይህ የእናትነት ፀጋ ነዉ ይህን በአላችንን የበለጠ ትርጉም የሚሰጠዉ። 

ማርያም ለመልአኩ የጌታ ባርያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ በማለት ሊያስከፍላት ከሚችለዉ ዋጋ በላይ ከፍላ የአለምን ሐጥያት የሚያስወግደዉን የእግዚአብሔርን በግ ወለደች ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሸ ተባለች።

ዛሬስ እኔና እናንተ ከሁኔታ በላይ አዳኙ በሰዎች ህይወት ዉስጥ እንዲወለድ እድል እያመቻቸንና እየሰጠን ነዉ? ለሔዋን የሚቀድመወ ተስፋ በተፈጥሮ መባዛት ሳይሆን ድል በነሳት ላይ ድል ማግኘት ነዉ። ዛሬ ሰዉ ሁሉ ድል ተነስቶ በሞት ፍርሀት ዉስጥ ባለበት በዚህ ወቅት የምስራች ልንለዉ ተስፋ እንዳለ ልናሳየዉ ይገባል።

መልካም የእናተች ቀን ይሁንልን።

 

ግንቦት 2 ቀን 2012 ዓ.ም

ቤተልሔም አበራ

©ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ ኢትዮጵያ። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።