መጣጥፎች

ሰላምን ፍለጋ ሰላምን ማሳደድ

ቤተልሔም አበራ

December 10, 2020

 

      ሁሉም በየቤቱ ሰይፉን እየሳለ፣

      አደባባይ ሲቆም ሰላም ሰላም  ካለ፣

     ሰዉ ራሱን እንጂ ማንን ያታልላል፣

    ይልቅ እግዚአብሔርን ቢማፀን ይሻላል።

              (ዘማሪ ታምራት ሀይሌ ቁጥር 6) 

 

የሰው ዘር በሙሉ ሰላምን በመፈለግ ላይ ነዉ።  ስለ ሰላም ብዙዎች ዘምረዋል፤  በርካቶችም አዚመዋል።  ስለ ሰላም ጥቂት የማይባሉ ጽፈዋል፤  አያሌዎችም ህይወታቸውን የመስዋዕት በግ አድርገዋል።

ሰላምን ፍለጋ አያሌዎች መንፈሳዊ ጉዞዎች አድርገዋል።  በአንጻሩ ሌሎች ደግሞ ሰላምን ሲፈልጉ የሱስ ተጋላጭ ሆነው በአጭሩ የነበራቸውን አንፃራዊ ሰላማቸውን አጥተው በመንገድ ላይ ወድቀዋል። አለያም ለዘላለም ሰላም ወደሌለበት ተሸጋግረዋል ። ሚሊዬኖችም ሰላምን ለመሻት ከአገር ከቄያቸው ተሰደዉ በየሰዉ አገራት ተንከራተዋል፤ የሰዉነትንም ስብእናና ክብር አጥተዋል።

ወላጆች የልጆቻቸውን ስም ሰላም፣ ሰላማዊት፣ ሰላሙ ብለዋል።  ከተሞችም  ሀገረ ሰላም፣ ፍኖተሰላም  ተብለዋል ።  አምልኮ ስፍራዎችን ደጀ ሰላም፣ ደብረሰላም በማለት የሰላም ምኞታቸውን ገልጸዋል ። 

ሀይማኖታትም በአንዱ ወገን አምነታችን የሰላም ሀይማኖት ነው ሲሉ፤  በሌላዉ ጎራ ደግሞ የእምነታችን ራስ የሰላም አለቃ ነው ሲሉም ተሰምተዋል።  

በአለም አደባባዮች መንግስታትና ሀገራት የሰላም ማስጠበቅ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል ።  ፊርማቸው ሳይደርቅ ለግጭት የተጋበዙ፣ የአደራዳሪና አስታራቂ ሽማግሌም የጠሩም በርካቶች ናቸው። ሰላምን ለማጽናት የሰላም ሚኒስቴር እስከማቋቋም ተደርሷል።

ለሰላም መታሰቢያነት አርማዎች በእርግብ ምስል ከአገራት ባንዲራ ጎን ለጎን ተውለውልበዋል።  ይሁን እንጂ የሰላም መጥፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ። መነሻ ምክንያቱም ከወትሮው ቀላልና ለመፍታት ዉስብስብና አስቸጋሪ  እየሆነ መጥቷል። አሁን አሁን ሰላምን ከማግኘት ይልቅ ሰላምን ማጣት ለሰው ልጆች ቀላል እየሆነ መጥቷል ።

የሰው ልጅ በምድር እየበዛ በመሄዱ ምክንያት የሀጢያት መረብ ከመቼውም ይልቅ ውስብስብና ለመበጠስ እስካይቻል ድረስ ጠንካራ አድርጎታል ።  እግዚአብሔርም ሰዉን በመፍጠሩ ሲፀፀት እናየዋለን ።

እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ።  እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ።(ዘፍጥረት 6:4)

አለም  ከዬትኛውም ክፍለዘመን ይልቅ በሰላም እጦት የተናወጠችበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ።  መላው አለም ያለ ልዩነት በነውጥና በግጭት ውስጥ ነው ።  በሰዉ ልጆች ታሪክ ሰዎች ሁሉ ያለልዩነት ሰላምን ይፈልጋሉ። ፍጥረት በሙሉ በሰዉ ልጆች ሰላም ማጣት ዋጋ እየከፈለ ነዉ። ሰላምን ማስጠበቅ የአንድ ወገን የቤትስራ አይደለም።  ይልቁን ለመጠናከርና ለመጠበቅ የሁለትዮሽ በጎ ፈቃድና ትብብር የሚጠይቅ ነገር ነዉ። 

በመሆኑም ምንም ያህል አለም ቢሰለጥን የሰላም ፍለጋ ከትላንት ይልቅ ዛሬ እየበረታ መጥቷል።  የሰዉ ልጅ ፈጣሪን ባለመታዘዝ በገዛ መንገዱ ለመሄድ ከወሰነበት ቀንና ሰአት አንስቶ በቀጥተኛው ግኑኝነቱ ማለትም ከፈጣሪው ጋር ብሎም በጎንዮሽ ግንኙነቱ ማለትም እርስ በርሱ ሰላሙ ደፍርሷል፣ ግንኙነቱም ተቋርጧል ።(ሮሜ 3:23)

ይህንም በዘፍጥረት ምእራፍ 3:12-13 ላይ ማየት እንችላለን። 

አዳምም አለ፡— ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ።

 እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን፡— ይህ ያደረግሽው ምንድር ነው? አላት። ሴቲቱም አለች፡— እባብ አሳተኝና በላሁ።

አዳም በአንድ ጊዜ ፈጣሪ እግዚአብሔርን እና የአጥንቱ ፍላጭ የስጋዉ ቁራሽ የሆነችዉን ሄዋንን ሲከስና የራሱን ሀላፊነት ላለመዉሰድ ሲያመካኝ እናየዋለን።  ሄዋን በበኩሏ አለመታዘዟን በእባብ ላይ ስታመካኝ እናያለን። በፈቃዳቸዉ ላለመታዘዝ በመረጡት ጎዳናና ከእግዚአብሔር ይልቅ ሴይጣንን ለማመን በወሰዱት እርምጃ ቅጣት አግኝቷቸዋል ። ሆኖም እግዚአብሔር ከመጀመሪያው ለሰዉ ልጆች ያቀደዉ ሰላምና ተድላ ግን ተቋረጠ። 

ይህ ተፈጥሯዊ የሰላም ኪዳን ስለተቋረጠ፤ ሰዎች በሰላም እንዲኖሩ አለም  የበኩሏን ጥረት ብታደርግም የመንግስታት፣ የአገራት፣ የአገልጋዮችና የሽማግሌዎች ጥረት ከንቱ ሆኖ ቀርቷል።  ተሳክቷል ተብሎ በሚታሰብባቸው ሁኔታዎች እንኳን አንፃራዊና ጊዜያዊ ሰላም ብቻ ነዉ ያለው። 

 

1. ሠላም ምንድን ነው ?

እንደ ኦክስፎርድ የቋንቋዎች ጥናት ገለፃ ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ወቅት ወይም ሁኔታ ወይም ያለመረበሽ ነፃነት  ማለት ነው።   እርቅ፣ ፀጥታ፣ እርጋታ የሚሉትን ትርጉም የያዘ ነዉ።

በመጽሐፍ ቅዱስ አፈታት Shalom/ሠላም፡ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል eirene ከሚለው የግሪክ ግንድ ቃል የመነጨ ሲሆን ሙሉነት ፣ ስኬት ፣ ቅንጅት፣  ሁለንተናዊ ደህንነት፣ የሚለውን የሰውንና የማህበረሰብ አጠቃላይ ቅኝት ይወክላል።  በመጽሐፍ ቅዱስ አተያይ  ሠላም የግጭት አለመኖር ማለት ብቻ አይደለም ።  ይልቁን የግጭት አለመኖር የሠላም መኖር ምልክት ነዉ እንጂ በራሱ ሠላም ወይንም የሠላም ምንጭ አይደለም። ሠላም ከሁኔታ የሚያልፍ እንደሆነ ይጠቁማል።

 

2.  የሠላም አይነትና ምንጭ

2.1. እግዚአብሔራዊ /ዉስጣዊ  ሠላም፦

የእግዚአብሔር ሠላም ወይም ውስጣዊ ሠላም የግለሰብን ውስጣዊ የደህንነት ዋስትና የሚወክል ነው።  ውስጣዊ ሠላም አለም እንደምትሰጠው በውጫዊ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ አይደለም ።  ይህ ሠላም ሰዎች በችሮታቸው የሚሰጡን ወይም የሚነሱንም አይደለም።

 

2.1.1.  ውስጣዊ ሠላም ምንጩ እየሱስ ነው ።

የግለሰቦች ውስጣዊ ሠላም የሚመሠረተው ከፈጣሪያቸው ጋር ባላቸዉ ጥብቅ ግንኙነት ነው ። ይህ የሠላም አይነት ባለቤቱም እግዚአብሔር  ነው ። በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሠላምህ ትጠብቃታለህ። (ት.ኢሳ 26:3)  ዉስጣዊ ሠላም የሰላሙ ባለቤትና ምንጭ በሆነዉ በእግዚአብሔር ላይ በመታመንና በመደገፍ የሚገኝ ነው ።

ውስጣዊ ሠላም የሚገኘዉም ከእግዚአብሔር ብቻ ነዉ።  ዉጫዊ አካል፣ የቁስና የማቴርያል ግኝት፣ እዉቀት፣ የፖለቲካ ድርድሮች ዉስጣዊና ዘላቂ ሠላም ሊሰጡን አይችሉም።  በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ።  በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።(ዮሐ .ወ 16:33)

ይሄ ሠላም ከዉስጥ ወደ ዉጪ የሚፈስ ነው ።  ሠላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።(ዮሐ.ወ 14:27)

ጌታ ኢየሱስ በዚህ ቃል ላይ እርሱ የሰላሙ ባለቤት መሆኑን ይናገራል።  ይሄንኑ ሰላም እተውላችኋለሁ በማለት ቃል ገብቶልናል ።  የእርሱ ሰላም ደግሞ በአይነቱም ሆነ በውጤቱ አለም ከምትሰጠው እንደሚለይ ይናገራል።

እግዚአብሔር አእምሮን የሚያልፍ ሰላም እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል (ፊልጵስዩስ 4:6)።  ማለትም ሁኔታን፣ ታሪክንና ነባራዊ አለምን የሚያልፍ ሰላም። የእግዚአብሔር ሰላም በአእምሮ ቀመር ላይ የተመሠረተ አይደለም።  አእምሮ በማናቸውም የስሜት ህዋሶቻችን የምናገኘዉን መረጃ ብቻ ነዉ የሚያምነዉ።  እግዚአብሔር ግን ከዚህ ከአእምሮ መረጃ በላይ የሆነውን ሰላም ነው እሰጣችኋለሁ ያለን።  የመጽሐፍ ቅዱስ ሰባኪያን እምነት ለአማኞች ስድስተኛው የስሜት ህዋስ ነው ይላሉ።  እንግዲህ ይህን ሰላም ያለ እምነት ልንለማመደዉ አንችልም ማለት ነው።

ስለዚህ የሰዉ ልጆች በጥረታቸዉ ይህንን ሰላም ማግኘት አይችሉም።  የሰላሙም ምንጭ እርሱ ከሆነና የሰላሙም አይነት ከአለም ሰላም የሚለይ ከሆነ ሁሉም ወደዚህ ጌታ በፈቃዱ መምጣትና በምድር መቶ እጥፍ ፤ በሰማይ ደግሞ ዋይታ፣ ለቅሶና ጥርስ ማፏጨት የሌለበትን የዘላለም ህይወት ሊያገኝ ዛሬም በሩ አልተዘጋም ፤ አስራ አንደኛዉ ሰአት ላይ ቢሆንም አልረፈደም።

 

2.1.2.  ዉስጣዊ ሰላም ኢየሱስ የሰላሙ አለቃ ነዉ

ኢየሱስ የሰላሙ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የሰላም አለቃ ነው ።  ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።(ት.ኢሳ 9:6)

በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።  አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል።

እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።

መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።(ኤፌ 2:12-18)

እርሱ የጥልን ግድግዳ በስጋዉ አፍርሷል።  በእኛና በእርሱ መካከል የነበረዉን ልዩነት በመስቀሉ ስራ ገንብቶታል።  በመስቀል ላይ በተሰራልን ስራ በቀጥተኛዉ መስመር፡ ሀጢያተኛዉ ሰዉ ከእግዚአብሔር ጋር ፣  በአግድመቱ መስመር፡ ሰዉ ከሌሎች ሰዎችና ከአከባቢዉ ጋር እርቅ አድርጓል።

በእርሱ ስራ አንድ የመሆን፤ ከጥል ወደ ፍቅር፣ ተጠርተናል።  የእርሱን ሰላም በውስጣችን በመሾም በተግባቦት ጤናማ ግንኙነት ልናጎለብት እንችላለን።  የእግዚአብሔርን ሰላም መለማመድ ለዚህኛዉም እና ለሚመጣውም አለም እጅግ ማትረፊያ ነዉ።

በመሆኑም ሰላምን ፍለጋ፤ ሰላምን ማሳደድ ትተን ሁላችንም የሰላሙን ንጉስ ጌታ ኢየሱስን በላያችን ላይ ልናነግስ ይገባል።  

    ሰላም ሰላም ሰላም፣

    ሰላም ሰላም ለአለም፣

    ለአለም ያለ እየሱስ የለም።

             ዘማሪ ታምራት ሀይሌ (ቁ 6)

 

2.2.3.  እግዚአብሔራዊ / ዉስጣዊ ሰላም ዘለቄታና ዋስትና አለዉ

ውስጣዊ ሰላም በእግዚአብሔር ባህሪ ላይ የተመሠረተ እንጂ በእኛ ሁኔታ የተቃኘ አይደለም።  እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።(ዮሐ .ወ 14:27)

ተራሮች ይፈልሳሉ፥ ኮረብቶችም ይወገዳሉ፤ ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አይፈልስም የሰላሜም ቃል ኪዳን አይወገድም፥ ይላል መሐሪሽ እግዚአብሔር።(ት.ኢሳ 54:10)

ዉስጣዊ ሰላም በምናየዉ በገሀዱ አለም ሁኔታ ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃልኪዳን ላይ የተመሠረተ ነው ። ስለዚህ እግዚአብሔራዊ ሰላም ከአእምሮ ስሌት፣ ከልብ ሀሳብ የዘለለ ነዉ።  ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።

           የማይደፈርስ ሰላም አለኝ፣

            ኢየሱስ የሰጠኝ፤

            መሠክራለሁ ለአለም ሁሉ፣

                  በፍራቻ በጭንቀት ላሉ።

                             ዘማሪ ዶ/ር ደረጄ ከበደ

 

2.2.4.  ውስጣዊ ሰላም በቃሉ ላይ የተመሠረተ ነው 

በቃሉና በእግዚአብሔር ሕግ የተጠመደ ሰዉ ሰላሙን የሚያደፈርስበት ሌላ ወጥመድ የለዉም ።

ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፥ ዕንቅፋትም የለባቸውም።(መዝ 119:165)

በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።(ኢሳ 26:3)

ውስጣዊ ሰላም የሚመሠረተውም የሚመነጨዉም ከእግዚአብሔር ቃል ነዉ። ህግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሀን ነዉ።  እንዳንሰናከልና እንዳንታወክ የሚመራን ነዉ። ስለዚህም በምንም አንናወጥም።

 

2.2.  አለማዊ/ ውጫዊ ሠላም፦

ውጫዊ ሰላም አጠቃላይ በማህበረሰብ ውስጥ የግጭት አለመኖርና መረጋጋት ሲያመለክት፤ በአንጻሩ ደግሞ የማህበራዊ ትስስር ፣ ተግባቦት መኖር ማለት ነው።  የበላይ ገዥነት ያለው የማህበራዊ እሴት መኖርን ያመላክታል ። ውጫዊ ሰላም የማህበረሰብን ሰላም የሚወክልና አንዱ በሌላው ላይ ተመጋጋቢነት ያለው ነዉ።

ዉጫዊ ጥያቄዎች ለውጫዊ ሰላም መታጣት ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ።  ለምሳሌ ክልል የመሆን፣ መንግስት የመሆን፣  የብሔር  መብት ጥያቄ፣ የድንበር ይገባኛል፣ የግጦሽ ቦታ፣ የቋንቋ ጥያቄዎች፣ የጾታ እኩልነት፣ የወንዞችና የግድቦች የበላይ ተጠቃሚነት፣ የኮቪድ-19 ክትባት የደሀና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የመሳሰሉት ይገኙበታል።

 

2.2.1. የአለም/ዉጫዊ  ሰላም ጊዜያዊ ነው 

...እኔ የምሰጠው ሰላም አለም እንደምትሰጠዉ አይደለም።(ዮሐ .ወ 14:27)

አለማዊ ሰላም ዘለቄታ የሌለዉና ጊዜያዊ ነዉ።  እንዲሁም ደግሞ ተነፃፃሪ እንጂ ፍፁምነት የለዉም።

የሰላም ምንጭ ነዉ ብለን ያሰብናቸዉ ነገሮች ሲሟሉ ጊዜያዊና አንፃራዊ ሰላም ስናገኝ ወዲያዉ በቅስበት ሀይል ሰላማችን ሲጓደል እናየዋለን። ለውጫዊ ሰላማችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች በራሳቸዉ ፍጹምነት ስለሌላቸውና በፍጥረታቸዉ አላቂ ስለሆኑ ቋሚና ፍጹም ሰላም ሊያስገኙልን አይችሉም።

 

2.2.2. የአለም/ዉጫዊ ሰላም በሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው 

ጊዜያዊና በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው።  ቅድመ ሁኔታዉ መሟላት ራሱ ለሰላሙ መረጋገጥ ዋስትና መስጠት አይችልም።

እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚያስቱ ነቢያት እንዲህ ይላል፤ በጥርሳቸው ሲነክሱ በሰላም ይሰብካሉ፤ በአፋቸው ግን አንዳች በማይሰጥ ሰው ላይ ሰልፍን ያስቡበታል።(ት.ሚኪያስ 3:5)

 

2.2.3. የአለም/ዉጫዊ ሰላም ስር ነቀል መፍትሔ የለዉም

አለማዊ ሰላም ለሰላሙ መታጣት መሠረት የሆነዉን ችግር አይፈታም።  እዉነተኛና ዉስጣዊ ሰላም ሳይኖር በመሸፋፈንና አቅጠጫ በማስቀየር(diversion than solution ) ላይ ያተኩራል።

ሰላም ሳይኖር፡— ሰላም እያሉ ሕዝቤን አታልለዋልና፤ አንዱም ሰው ቅጥር ሲሠራ፥ እነሆ፥ ገለባ በሌለበት ጭቃ ይመርጉታልና። (ት. ሕዝ 13:10)

የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን፡— ሰላም ሰላም ይላሉ። (ት.ኤር 6:14)

ይህ አለማዊ ሰላም በአጠቃላይ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ለሰላም መታጣት የአንበሳዉን ድርሻ የሚወስደውን የሰዉ ልጅ ሀጢያተኝነትን አይጠቁምም አያክምም።  ከበሽታዉ ይልቅ ምልክቶችን በማባበል ላይ ጊዜና ጉልበት ያጠፋል።

ውጫዊና ውስጣዊ ሰላም ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ ናቸው።  የውስጣዊ ሠላም መኖር ወይም መታጣት በውጫዊ ሠላም ላይ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ያሳድራል ።  በመሆኑም የአንድ ግለሰብ ውስጣዊ ሰላም ማጣት ከራሱ ጋር ብሎም ከአከባቢውና ከፈጣሪው ጋር ሰላም ወደማጣት ያመራል።  ስለዚህ የዉጫዊ ሰላም መሠረቱ የግለሰቦች ውስጣዊ ሰላም መጠበቅ ነዉ።  ከእግዚአብሔር ጋር ተስማማ ሰላምም ይኑርህ በዚያም በጎነትን ታገኛለህ።

 

3. ሰላምን በማስጠበቅ የአማኞች ሚና

ክርስቲያኖች የሰማዩን መንግስት የሚወክሉ በምድር የሚኖሩ የእግዚአብሔር አምባሳደሮች ናቸዉ።  አምባሳደር የራሱን አገር በመወከልና የአገሩን ጥቅም በማስከበር፣በሌላ አገር የሚኖር ዜጋ ነዉ።  ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ጥሪ ከደረሳቸዉና ለጥሪዉ ምላሽ ከሰጡ በኋላ (ዮሐ ወ 1:12)  በዋጋ ስለተገዙ የራሳቸው አይደሉም። የራሳቸውን አጀንዳም መፈፀም አይገባቸውም። በመሆኑም ለሰማይ መንግስት ጥቅም በምድር እንደሚኖር ተወካይ ነዉ። አገሩ ለመግባት እየናፈቀ ተልእኮዉን በአግባቡ የሚወጣ ነዉ።  እንደ አምባሳደር ሲኖር በምድር ቆይታዉ እንደ አማኝ ሊያከናውናቸውና እንዲወክላቸዉ ከተሰጡት ሀላፊነቶቹ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸዉ።

 

3.1. የሰላም ወንጌል መጫማት (ኤፌ 6:14-15 : ሮሜ 10:15)

እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤

አማኝ በሚሄድበት ሁሉ ይህን የሰላምወንጌል፣ የክብር ወንጌል በአለም ዙሪያ ሁሉ ይሰብክ ዘንድ አደራ አለበት።  መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው።  

የምስራቹን ወንጌል መናገር፣  የሰላምን ወንጌል መጫማት፤  የሰላም ሰዉ መሆንን ይጠይቃል።  የህይወት ተምሳሌትነት የሌለበት " ፍየል ወዲህ… ቅዝምዝም ወዲያ" ከሆነ ክርስትና አስቸጋሪ ይሆናል።  ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ እንደማይወጣ ሁሉ ሚናችንን መለየ፣ ሚዛናችንን መጠበቅ፣ ወገንታዊነታችንን ሰማያዊ ማድረግ ያስፈልጋል።

ሸክም ይሰማሀል ወይ? ክርስቲያን ወንድሜ ሆይ፣

ለሚጠፉት ወገኖች ልብህ ያዝንብሀል ወይ?

ጥፋታቸዉ ተሰምቶህ አዝነህ ትጸልያለህ፣

በራስህ ተመክተህ ወይስ በመፍረድ ላይ ነህ?

                    ዘማሪ ደ/ር ደረጀ ከበደ

 

3.2. አስታራቂ መሆን፡ የሚያስታርቁ ብፁአን ናቸዉ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። (ማቴ 5:9)

የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ሰዉን በክርስቶስ እየሱስ የመስቀል ላይ ስራ በወንጌል የምስራች የሚያስታርቁና በዚያዉ ብስራት ሰዉን ከሰዉ ጋር የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸዉ።

አምላካችን እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነዉ። ሰላምን ለማምጣት የሚጥሩ አስታራቂዎች የአምላካቸዉ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ።  የአማኞችም ዋነኛዉ ጥሪና ተልእኮም ይሄዉ ነዉ። የእግዚአብሔር ልጆች የአስታራቂነት ሚና በአግባቡ ለመወጣት የሚከተሉትን እንደ መርህ ቢከተሉ መልካም ይሆናል ደግሞም የእግዚአብሔርን ሀሳብ ይወክላሉ።

3.3. እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤(ምሳ 6:16-19)

 

 • ትዕቢተኛ ዓይን፤

 እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። (1ጴጥ 5:5: ያእቆ 4:6)

ትእቢተኝነት ከእኔነት ምንጭ የሚቀዳ ነዉ። እኔ አዉቃለሁ፣ ከእኔ በቀርና በላይ የለም።  በትእቢተኛ አይን ፊት ሌላዉ ሁሉ ለምንም ነገር ብቁ አይደለም።  ሌላው ቢኖር የማይጠቅም፣ ቢሞት የማይጎዳ ነዉ። ስለዚህም በትእቢት የተወጠረ ነዉ።  ትእቢተኛ በዘሩ፣ በእዉቀቱ ፣ በመልኩ፣ በኢኮኖሚው ይታበያል። እግዚአብሔር ግን ይቃወማቸዋል። ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ደግሞ ይደቃሉ።  

የሀማ ሚስት ይህ በፊቱ መዉደቅ የጀመርክለት ሰዉ አይሁዳዊ ከሆነ ፈጽሞ በፊቱ ትጠፋለህ እንጂ አትለማም እንዳለችዉ ከእግዚአብሔር ፍጥረት ጋር መታገልና ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ፈጽሞ ለጥፋታችን እንጂ ለልማትና ለሰላም አይሆንም።  በተቃራኒዉ ግን እግዚአብሔር ትሁታን ትህትናቸዉን የሚኖሩበት ጸጋን ይጨምራል።

 

 • ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥

 አስርቱ ትእዛዛት በጥቅሉ በሦስት ይከፈላሉ። (ሰዉ ከፈጣሪ ጋር፣ ሰዉ ከራሱ ጋርና ፣ ሰዉ ከሰዉ ጋር) የሚኖረዉን ጤናማና ሚዛናዊ ግንኙነት የሚወስኑ ናቸዉ። አትግደል ከእነዚህ መሀል ስድስተኛዉ ትእዛዝ ነዉ። በሀምሳለ እግዚአብሔር በእጆቹ ስራ የተፈጠረውን ክቡር የሰዉ ልጆች ደም እንዳናፈስ ምክርና ማባበል ሳይሆን ህግና ድንጋጌ ብሎም ተመጣጣኝ ቅጣት ጭምር መጽሐፍ ቅዱስ ያስቀምጣል። ደም የሚያፈስ ደሙ ይፈሳል በማለት።  ዘንድሮ ይህን ትእዛዝና የሚያስከትለውን ቅጣት ችላ ብለን በልባችን ምሻት በአይናችን አምሮት ከህሊና ፍርድ እንኳን አፈንግጠን ከሄድን የአለም የቴሌቪዥን መስኮቶች ዝንጉ ያልሆኑ ምስክሮች ናቸዉ።  

ጥላቻ ግድያን ትቀድማለች። ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነዉ ይላል መጽሐፉ ። በአጠገብህ ያለውን ወንድምህን ሳትወድ ያላየኸኝን እኔን እንዴት እወዳለሁ ትላለህ? የእግዚአብሔር ፍቅር ከእኛ ጋር በሚኖረው በሀምሳለ እግዚአብሔር በሆነዉ ሰዉ ውስጥ ነዉ የተገለጠዉ። አሁን ባለንበት ዘመን በእኛ ውስጥ የነበረዉ የእግዚአብሔር ፍቅር በዘረኝነት፣ በጎሳ፣ በቀለም፣ በሀይማኖት ተሸርሽሮ ህያውነት የሌለን ከሆንንና፤ በእግዚአብሔር አይን ትዝብት ላይ ከወደቅን፤  ለቅጣት ራሳችንን ካመቻቸን፤ ልባችን  የፍቅር ትርታ መምታት አቁሞ በጥላቻ መጠውለግ ከጀመረ ለእርዳታ እንኳን የዘገየ ሆኗል።

ከህሊና ፍርድ፣ ከህግ መዝገብ አምልጠን ይሆናል። ለሁሉ እንደስራዉ ልሰጥ ዋጋዉ ከእኔ ጋር ነዉ ያለዉ ጌታ ግን አይዘበትበትም ። የዘገየ ቢመስልም ይመጣል። ያላየ፣ ያልሰማ ቢመስልም በጽድቅ ይበይናል።

 

 • ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፥

መጽሐፍ ቅዱስ ልበ ንፁሐን እግዘብሔርን ያዩታል ይላል። እግዘብሔርን ማየት የሚቻለዉና የሚገኘዉ በልብ ንጽሕና ነዉ። ሰዉ ፊትን ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል። ዛሬ አማኞች እግዚአብሔርን ከማየት የከለከለን፣ በልባችን መኖሪያዉን እንዳያደርግ በእያንዳንዳችን ውስጥ ጌታ ቤት እንዲለቅ ያስገደደዉ ምን ይሆን? ጌታን ከእኛ ጋርና በእኛ መሀከል ከመኖሮ ያሸሸዉ? እርሱ አምላካችን እኛ ህዝቦቹ እንዳንሆን በመካከላችን የጥል ግድግዳ የሆነዉ ነዉሩ የአፋችን ቃልና፤ አጸያፊዉ የልባችን ሀሳብ ዬቱ ነዉ? የክርስቶስ ልብ አለን እያልን መፈክር አንግበን፣ ጥቅስ ለጥፈን ልባችንን ግን ወንድምን አሳልፎ መስጠት የይሁዳ ሀሳብ፤ ራስና ገንዘብ ወዳድነት የተቆጣጠረው ?።  የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና።  የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና። ስለዚህም እንደ አማኝ የአስታራቂነት የአምባሳደርነት ሚናችንን ለመጫወት መሀሪ፣ ይቅር ባይና ርህሩህ ልንሆን ይገባናል።

 

 •  ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥

እግርህን ከከፉ መንገድ ጠብቅ። እግራችን የሰላም ወንጌል ሊጫማ፣ የምስራቹን ለማውራት እኔን ላከኝ ብሎ ለመላክ የተዘጋጀ መልእክተኛ እንዲሆን እንጂ የጥፋት ጎዳናን ተከትሎ እንዳይነጉድ የአማኝነት ሀላፊነቱ ነዉ። ወደ ክፋትና የክፋት አስፈጻሚነት የምትሮጥን እግር እግዚአብሔር ይጸየፋል። ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም። የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።  በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?

 

 • በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ። 

   

በባልንጀራ ላይ በሀሰት አለመመስከርን 

በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።(ዘጸአት 20:16-17)

ለግላዊ ጥቅም ብለን በባለእንጀራችን ላይ ሀሰትን አለመናገር ለሰላም መጠበቅ መሠረታዊ ነዉ። ይልቁኑ ባልንጀራህ ከአንተ እንዲሻል በትህትና ቁጠር። ለወንድምህ ቅድሚያ ስጥ ነዉ የቅዱስ ቃሉ ምክር። በሀሰት ጠብን ከመዝራት መታቀብ የአማኞች መብት ሳይሆን መሠረታዊ ግዴታ ነዉ። ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤

 

 • መፀለይ

እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ።(1ጢሞ 2:1-2)

 የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ 

ፀሎት የራሳችንን ፈቃድ ለማስፈጸም የእግዚአብሔርን እጅ በትህትና የምንጠመዝዝበት፣ ፊርማ ማሰባሰቢያ አይደለም። የሰላምን ሂደት ለማስጠበቅ አማኝ ያለወገንታዊነትና መድሎ ለሁሉ መፀለይ ይኖርበታል።  ስለዚህ በሰማይ ያለችዉን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በምድር ለማስፈጸም መጸለይ አለብን።

 

 • መገሰጽ

የአማኝ ሌላኛዉ የአምባሳደርነት ተልእኮ መሪዎች፣ ምእመናን ሲያጠፉና ህዝብ መረን ሲወጣ መገሰጽ ነዉ። የፖለቲካ መሪዎች በዘረኝነት፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አመለካከታቸዉ በጠበብተኝነት ይሁን በትምኪተኝነት ስተዉ ሲገኙ መመለስ፣ መምከርና መገሰጽ ይጠበቃል። በመንግስትና በህዝብ በተለይም በወጣቶች የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን ለማርገብ የበኩሉን ሊወጣ ይገባዋል።

የሀይማኖት አስተማሪዎች፣ አማኞች ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ አስተምሮ ሲያራምዱ፤ ለሰው ጥቅም፣ ለእግዚአብሔር ክብር የማይሆኑ ፖሊሲዎችና አስተምሮዎች ሲቀረጹ ዝም ብሎ ማየት አይኖርበትም።

በአንጻሩ ግን በወንጌላዊያን አማኞች ቤተክርስቲያን እምነታቸዉን በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ላይ ያደረጉ፣ የሰላሙ ንጉስ በልባቸዉ እንዲኖር የፈቀዱ፤  በቁሳዊ ፍላጎቶቻቸዉና በስልጣን ጥም፡ ይህን የክብርና የሰላም ወንጌል  አቃለዉ እርቅና ዳኝነት ፍለጋ በአለም አደባባዮች መዋላቸዉ፣ ወንጌልን የምስራች ብሎ ርቀዉ ላሉት ለመናገር እንቅፋት ቢሆንብንም የህይወት ተምሳሌትነታችን የወረደቢሆንም፣  ዛሬም እየሱስ የሰላም ምንጭና የሰላም አለቃ ነዉ።

በሌላኛዉ ጎራ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ምእመናኖቿ ለዘመናት የአገርን ሰላምና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በመጸለይና ጾምን በማወጅ፣ የሽምግልና ሚና በመጫወት፣ ከአስተምሮ የተለየ ነገር ሲመጣ ደፍሮ በማዉገዝ በእምነቱ ላይ ቀጥተኛና በአገራችን ላይ ተዘዋዋሪ የሆነ በጎ ተጽእኖ ያሳደረችበትን ወቅት ሳላመሰግን አላልፍም ሌሎቻችንም አርአያነቱን እንድንከተል ጥሪዬን አቀርባለሀ።

 

4.  የሠላም መኖር መገለጫ ምንድን ነዉ?

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡— ዳግመኛ ሽማግሌዎችና ባልቴቶች በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ፤ ሰውም ሁሉ ከዕድሜው ብዛት የተነሣ ምርኩዝ በእጁ ይይዛል።

የከተማይቱም አደባባዮች በእነዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ።(. ዘካርያስ 8:4-5)

 

4.1. የእድሜ ባለፀጐች በአደባባይ መቀመጥ

"ዳግመኛ ሽማግሌዎችና ባልቴቶች በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ።"

የእድሜ ባለፀጎች በአደባባይ መታየት ስል፤ ታዲያ ብርቅሽ ነው ? እንዴ ጎዳናዉን የሞሉት እነማን ናቸውና እንዳትሉኝ።

ችግር ገፍቶ አደባባይ ያወጣቸውን፣ ልመና አንገት ያስደፋቸዉን፤ አጉራሽ አልባሽ፣ ጧሪ ቀባሪ ያጡትን ማለቴ አይደለም ። አባይን በጭልፋ ቢሆንባቸውም የበኩላቸውን ለማድረግ በግልም በተቋምም  እየታተሩ ያሉትንም፤ አዛዉንቶችን ከመንገድ ላይ በማንሳት እንዲጦሩ ከዚያም የክብር ሞት እንዲሞቱ ለማስቻል የሚጥሩትን የበኩላቸውን የሚያደርጉ ዉድ ዜጎችን በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግን አላልፍም ።

ሰላም በተግባቦት፣ በጭውውት፣ በመጋራት የተሞላ ነው ።  ከላይ በተጠቀሰዉ ክፍል ነብዩ ዘካሪያስ ያየው ራእይ እግዚአብሔር ዳግመኛ ኢየሩሳሌምን ሲያስባት የሚሆነውን ነው።  

ሰላም ሲኖር ስጋት፣ ፍርሀት የለም። ከእድሜያቸዉና ከድካማቸው የተነሳ የሌሎች እገዛ የሚያስፈልጋቸው አቅመ ደካሞች እንኳን በየበሮቻቸዉ አደባባይ ተቀምጠዉ የቀድሞውን የጥንቱን ያወጋሉ።  እሴቶች ይጋራሉ።  ለልጅ ልጆቻቸዉ ፍቅርን ያስተምራሉ ።  በታሪክ፣ በተረት የአገርን ገድል ይተርካሉ፣ ታሪክን ያስቀጥላሉ።

በእኔ እድሜ እንኳን ማህበረሰባችን በፍጥነት እየተለወጠ መምጣቱ አያከራክርም።  ድሮ ድሮ ልጆች የተወለዱበት ቤተሰብ አባል ብቻ ሳይሆኑ የተገኙበትም ማህበረሰብ አካል ነበሩ።  በመሆኑም ባህላችን፣ እምነታችን፣ አስተዳደጋችን ጭምር የማህበረሰቡ ነፀብራቅ ነበረ።  ልክ እንደ ጠቀስኩት ቃል አዛውንቶች በጋራ በአደባባዮች ላይ ያወጉ ነበር።  የንባብ ባህላችን ደካማ በሆነባት እንደ እኛ አገር ታላላቆች ቋሚና ህያዉ የታሪክ መጽሐፍት ነበሩ።

መኖራቸው የሰፈር አድባር የተባሉ የተከበሩና የታፈሩም ነበር።  ወላጆች በቤት ባይኖሩም ከሰፈር አዛውንቶች መገኘት የተነሳ ትዉልዱ ከጥፋት የታቀበ ነበር።

ዛሬ በሰላም መታጣት ምክንያት አዛዉንቶች ያለጧሪ ቀባሪ የቀሩበት፣ ከኖሩበት ቄዬ ተፈናቅለዉ ለረሀብ ፣ እንግልትና ስደት የተፈራረቀባቸዉ ዘመን ላይ እንገኛለን። ከዚህም የተነሳ ጉስቁልና የበዛበት፣ በእምባ ሲቃቸዉ አይናቸዉ የተከደነበት፣ ልባቸዉ ተሰብሮ አንደበታቸው ለእርግማን የተከፈተበት፣ ፈጣሪ በሀዘን ለቁጣና ቅጣት ከመንበሩ የተነሳበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።

 

4.2.  ረዥም እድሜ መኖር

"ሰውም ሁሉ ከዕድሜው ብዛት የተነሣ ምርኩዝ በእጁ ይይዛል።"

የሰው ልጅ በፈቃዱ ወደዚች አለም እንዳልመጣ ሁሉ በፈቃዱም ወደ መጣበት አይመለስም።  አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ እንደሚል ነፍስም ወደ ፈጣሪዋ፣ ስጋም ወደ አፈሩ መመለሱ አይቀርም።

ድሮ ድሮ ከማህበረሰባችን ኋላቀርነትና ንቃተ ህሊና ማነስ ጋር ተያይዞ እርግማን የተለመደ የህይወታችን የአርባ ቀን እድላችን ነበረና እድሜህ ይጠር፣ በአጭር ያስቀርህ፣ ትልቅ አትሁን፣ ወግ አትይ የሚሉና ሌሎች እርግማኖች የአንድ ሰዉ የእድገቱ አካል ነበሩ።

ፈጣሪ ከወሰነለት ቀነ ገደብ በእድሜ ማራዘሚያ መድሐኒት፣ በመጨነቅና በመጠበብ እድሜውን ከፍ ማድረግ ወይም  ማሳጠር የተቻለው የለም ።  ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?(ማቴ 6:27)

እግዚአብሔርም፡— መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ፡ አለ። (ዘፍጥረት 6:4)

ዘመናችን ሁሉ አልፎአልና፥ እኛም በመዓትህ አልቀናልና፤ ዘመኖቻችንም እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ።

የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፥ እኛም እንገሠጻለንና።(መዝ 90:9-10)

በረዥም እድሜ መባረክ የአንድ ሰላማዊ ማህበረሰብ መገለጫ ነዉ። ረዠምን እድሜ ከተድላ ጋር ማግኘት ከፈጣሪ የምንታደለዉ ችሮታ ብቻ ሳይሆን አንዲት ሉአላዊ አገርና መንግስት የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅና በቂ አቅርቦትና ምቹ መኖሪያ በማስገኘት የመሚመጣ ነዉ። 

ከሠላም መታጣት፣ ከኑሮ አለመመቻቸት ጋር ተያይዞ የሰዉ ልጆች እድሜ ሊያጥር ይችላል።  ለእድሜ ማጠር ቁሳዊና ተፈጥሮአዊ ነገሮች የበኩላቸዉ አስተዋጽኦ ቢኖራቸዉም በአንዳንድ ሁኔታ ውስጥ ግን ረጅምን እድሜ ልንጎናጸፍባቸዉ የምንችላቸዉን  መንገዶች መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል።

 

4.2.1.  እናትና አባትን በማክበር

አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።(ዘፀአት 20:12)

መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት።(ኤፌ 6:2-3)

ወላጆችን ማክበር ለእድሜ መርዘም ምክንያት ነዉ። ወላጃዊነት ሰፊ ሀሳብ ነዉ።ወላጅ ስንል ታዲያ በጣም ጠባቡን የቤተሰብ አባላት የያዘችዉን ብቻ አይደለም። የሰዉ ዘር የተዋልዶ ሰንሰለት ስንመለከት ሁሉም ወላጅ ነዉ። የኋሊት ከቆጠርን አያት፣ ቅድመ አያት፣ ቅምቅም....እያለ ወደ መጀመሪያው ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት ልዩነት ወደማይንፀባረቅበት ወደ ሰዉ ልጆች አባት ወደ አዳም ከዚያም የሰዉ ልጆች ምንጭ ወደሆነው እግዚአብሔር ይጠቁመናል።  በመሆኑም ከእኛ አንድ እርከን ከፍ ለሚሉት ወላጆቻችን ብቻ ሳይሆን ለሰዉ ዘር በሙሉ በተለይም ለታላላቆች ከበሬታ ያስፈልጋል። ሁሉን ልናከብር፣ ልንወድ፣ ለባልንጀራችን የሚገባዉንና የሚያስፈልገውን ልናደርግላቸው ይገባል።

ይህን የሚያደርግ ትዉልድ በሀገራችንም ወግ "የማታ እንጀራ ይስጥህ…. ፈጣሪ አለሁ ይበልህ" የሚል ምርቃት ያገኛል።  በዚህም እግዚአብሔር ከጥንት በአብሮነትና በሰላም ውስጥ የፈቀደዉን በረከት እንቋደሳለን። የዘራነዉ በብዙ እጥፍ ስለሚበቅል እኛንም የእድሜ በረከትና ተድላ ይከተለናል። ረዥም እድሜ እንጠግባለን። 

 

4.2.2.  በመታዘዝና እግዚአብሔርን በመፍራት  

በመታዘዝና እግዚአብሔርን በመፍራት እድሜን ማስረዘም ወይም ባለመታዘዝ እድሜን ማሳጠር እንዳለ ግን ቅዱስ መጽሐፍ ያመላክታል። (ዘዳግም 28)

እግዘብሔርን መታዘዝ እድሜ እንደሚያረዝም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለዉ። እሺ ብትሉ ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ።   እሺ ባትሉ ባትታዘዙ ሰይፍ ይበላችኋል።  እግዚአብሔርን መፍራትና መታዘዝ ለዚህኛዉ አለም ብቻ ሳይሆን ለሚመጣውም የእግዚአብሔር መንግስት ይጠቅማል።

 

4.2.3.  በመፀለይና ልመና በማቅረብ(ት.ኢሳ:38:1-5)

በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ለሞት እስኪደርስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ፡— እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡— ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል፡ አለው።

ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡— አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ። ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ።

ሂድ፥ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፡— የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡— ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ አሥራ አምስት ዓመት አጨምራለሁ።

እዚህ ጋር ልብ ልንለዉ የሚገባዉ  ሕዝቅያስ በከንቱ አይደለም የእድሜ ጭማሪ የጠየቀዉ።  ከበፊት የነበረዉን እዉነተኝነት፣ የልብ ንጽሕና እንዲሁም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሰዉ እንደነበረ ገልጾ ነዉ።  እግዚአብሔርን  አንድ ነገር እንዲያደርግልን ስንጠይቅ ለምን? ከዚህ በፊት በተሰጠን እድሜ ምን አደረግንበት? ምን የኋላ ታሪክ አለን? ለነገ ዋስትና የሚሰጥ ምን የኋላ ታሪክ አለን  የሚለዉ ሊታሰብበት ይገባል። አንዳንድ ሰዉ ረዥም እድሜ በምድር ላይ መኖር ይመኛል። በእድሜዉ ላይ ግን ምን ሀሳብ አለዉ?።  በዘመናችን ላይ መሰልጠን እንድንችል ግን እናውቅ ዘንድ ዘመናችንን መቁጠር አስተምረን ብሏል መዝሙረኛዉ ዳዊት።

በሳይንሱ አለም ሰዉ ረጅም እድሜ እንዲኖረው አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሉ። ምግብ፣ የመኖሪያ አከባቢ ፣ የአየር ንብረት ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የጤና ሁኔታ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸዉ።  የሰላም መኖር አንዱ መታወቂያዉ ዜጎች በረዥም እድሜ መባረከቸዉ ነዉ።

በምእራባውያን አገር ሰዎች ከላይ በጠቀስኳቸው ሳይንሳዊና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ረዥም እድሜ ይኖራሉ ።  ከዚህም የተነሳ የራሴ የሚሉት ከእነሱ ጋር ሆኖ የምድሩን መንገድ ሁሉ እስኪጓዙ፤  ከዚያም በመልካም ሽምግልና እንዲያንቀላፉ የሚረዳቸዉ በማጣት የኋለኛዉን ዘመናቸዉን በነርሲንግ ሆም ዉስጥ ለመጨረስ የሚገደዱም አልጠፉም።  አንዳንዴም ለህክምና እርዳታ የሚሰጣቸውን የኦክስጅን እርዳታ እንኳን እንዲቋረጥ በቅርብ ሰዎቻቸዉ ይጠየቃል።

በአንጻሩ  ደግሞ ጦርነት፣ ረሀብ፣ ስደት፣ የጤና ችግር ለእድሜ ማጠር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ።  ረሀብ፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ በስብእናና በማንነት ማፈር፣ ከባሰም በአጭር መቀጨት የእለት ተእለት ዘይቤ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነዉ።  እድሜ ጠግቦ ድጋፍ ምርኩዝ መያዝ ቀርቶ፣ ሮጦ ሳይጠግቡ እንደወጡ መቅረት፣ ደግሞ ዛሬ ምን ይሆን ብሎ የቀኑ ክፋት(ማቴ 6:28) እስኪከፈት መጠባበቅ የእለት እንጀራ እየሆነ መጥቷል።

ልጆች ያለአሳደጊ፣ አዛዉንቶች ያለ ጧሪ ቀባሪ፣ አገር ያለተረካቢ ትዉልድ እያዘመመች ነዉ።  በአለም አቀፍ ደረጃ ታዳጊዋ በመባል የምትታወቀው ሀገራችንም ገና እንጭጭ በሆነዉ ኢኮኖሚዋ ምክንያት ብቻ ሳይሆን አድገዉ ለእድሜ ባለጸጋነት ለመድረስ ያልታደሉ ልጆቿንም እድሜ ለማመላከት ጭምር ነው  ይሄ ታዳጊዋ የሚል ስም የተቸራት።  አሁን ግን እያገረሸ ከመጣዉ የሰላም መታጣት፣ የእርስ በርስ ጦርነቱ ካስከተለዉ ስደተኝነት የተነሳ ታዳጊ ብቻ ሳይሆን ስደተኛ፣ ጎስቋላ፣ የእድገት መቀንጨር ያጋጠማት፣ የኋሊት የምትጎተት አገር ሆናለች።

4.3.  የሚጫወቱ ልጆች በአደባባይ መኖሮ

"የከተማይቱም አደባባዮች በእነዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ።"

ከላይ ባየነዉ ክፍል ነቢዩ ዘካሪያስ ያየዉ ራእይ ላይ ሦስተኛዉ የሰላም መኖር ማብሰሪያ መንገድ የልጆች በአንድነት መጫወት ነው ። 

ጨዋታ የሰዉ ተፈጥሯዊ ገጸ በረከትና የልጆች አለም አቀፋዊ መግባቢያ ቋንቋ ነው ።  ልጆች በዬትኛውም ስፍራ ሲገናኙ ያለ ልዩነት በጨዋታ ሲግባቡ እናያቸዋለን ።

በጨዋታ ውስጥ ዘር፣ ቀለም፣ ኢኮኖሚ ፣ ሀይማኖት ፣ ፃታ፣ ስፍራ የላቸውም ።  በእኔ የእድሜ ክልል እንኳን የሰፈር ልጆች በአንድነት ይጫወቱ ነበር።  አበባየሆሽ፣ ቡሄ መጣ እየተጫወትን በዚያ ውስጥ ባህልና እሴት እየተጋራን ነበር ያደግነዉ። ዬትኛውም ልዩነታችንን ተገንዝበንዉም ሆነ እክል ሆኖብንም አያዉቅም።  በጫወታ በዳበረ ግንኙነት ልጆች አብሮ አደግ ብቻ ሳይሆን ወንድም እህት የሚሆናቸው፤  ውሎ ካደረም የትዳር አጋር የሚሆናቸው ከዚያው ነበረ።

ምን ይሆን መጪውን ትዉልድ ተረካቢዉን የምናወርሰው?  በማህበረሰብ ቢሆን በየእምነት ተቋሞቻችን እሴቶች ጠፍተዉ የሰዉ ሀገር ባህል ወርሶን ስልጣኔአችን እድገታችንን የቀደመዉ።

ኢትዮጵያ አገራችን ታዳጊና የታዳጊ ልጆች አገር ናት።  ከአጠቃላይ ህዝባችን 44% የሚወክሉት እድሜያቸው ከ 14 አመት በታች የሚሆኑት ናቸዉ።  ይህ የእድሜ ክልል ለብዙ ሰዉ ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጋላጭ የሚሆኑበት ነው ።  የጎዳና ተዳዳሪነት ከእነዚህ አደጋዎች ትልቁን ድርሻ ይይዛል ። አደባባዮቻችንንም የሞሉት እነዚህ ጎዳና ነዉ ቤቴ፣ ድህነት አባቴ፣  ችግር ጎረቤቴ የሚሉ ፤ እግዚኦ ወላድ በድባብ ትሂድ የሚያሰኙ ልጆች እንጂ፤  በደስታ የሚቦርቁ፣ በጨዋታ የፈነጠዙ፣ ማታና ነገ የማያሳስባቸዉ ልጆች አይደሉም።

አሁን አሁን ሰፈር ላይ በአንድነት የሚጫወቱ ልጆች ማየት የተረት  ተረት (fairytale ) ካራክተር እየሆነ መጥቷል ።  ለዚሁም ችግሩ የማህበረሰባችን የባህል እየተቀየረ መምጣት፣ የአከባቢዎቻችን በቤቶች ታጭቀዉ ሰውን እንደ ቁስ ለማድረግ የሚቃጣቸዉ መሆን፣  በየሰፈሩ የተዘጋጀ የመጫወቻ ሜዳ አለመኖር፣  በአንጻሩ ደግሞ ከማህበረሰቡ በኢኮኖሚም ይሁን በባህል ተገልለዉ በታጠረዉ ጊቢያቸዉ ውስጥ የሚያድጉ ልጆች መበራከት፣ የባህል ወረርሽኝ፣ የማህበራዊና ማስ ሚዲያ ተጽዕኖ፣  የሰላም መታጣትና የሰዉ ልጆች በልዩ ልዩ አጀንዳ መከፋፈል ይገኙባቸዋል ።

አይ ድሮ ብለው ስለ ድሮ ከሚያዜሙትና ድሮ ላይ ፖዝ ካደረጉት ጎራ ሆኜ ሳይሆን  ለውጥ ካሻን ለለውጥ ከታገልን ከድጡ ወደ ማጡ ለመሄድ፣  ትሻልን ፈትቼ ትብስን አገባሁ ለማለት ሳይሆን የተሻለ ነገ፣ ቀና ማህበረሰብ፣ ያ! ሀይማኖተኛ የታፈረ፣ የተከበረ እግዚአብሔርን የሚያፍር ፤ ሰውን የሚያከብር ትውልድ ናፍቆኝ ነዉ።

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ የዛሬ ትዉልድ አልኩ እንጂ የዛሬውስ ወላጅ ቢሆን ፦

በልቡ በውሎዉ ከእግዜሩ ሸሽቶ፣

ቁሳቁስና ዝናን፣ ገንዘብ ተንተርሶ ፣

እርሱ ያልሰራበት ትውልድ፣  በብዙ ሲበዘበዝ፣ 

የኋሊት ቢመለስ የዘለለውን፣ ትምሀርት ለመከለስ፣ 

የሀይማኖት አባቶች መስቀሉን አሳልመው፣ 

እምነቱን ቀብተው፣

ቁራኑን አስተምረው፤ ጾም ፀሎት አስይዘው፣

ቢሞክሩት ምለው አስገዝተዉ ለመመለስ፣

ለካ በጣም ረፍዷል ለማቅናት ለመግራት፣

ነበረ እንጂ ያኔ ገና በለጋነት፣

ክፉዉን ከበጎዉ በደንብ ለመለየት ።

 

5.  የሰላም ዉጤት 

 

5.1.   በዙሪያችን እረፍት ይሆናል

የሰው አካሄድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘው እንደ ሆነ፤ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል።(ምሳሌ 16:7)

ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፥ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል።

ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፥ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል።

የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጕድጓድ ላይ ይጫወታል፥ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል።( ት.ኢሳ 11:6-8)

 

5.2.  የእግዚአብሔር ቤት ይሰራል

እግዚአብሔር ከእግሩ በታች እስኪጥልለት ድረስ በዙሪያው ስለ ነበረ ሰልፍ አባቴ ዳዊት የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት እንዳልቻለ አንተ ታውቃለህ። አሁንም አምላኬ እግዚአብሔር በዙሪያዬ ካሉት ዕረፍት ሰጥቶኛል፤ ጠላትም ክፉም ነገር የለብኝም።

እነሆም፥ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት፡— በአንተ ፋንታ በዙፋንህ ላይ የማስቀምጠው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል ብሎ እንደ ነገረው፥ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራ ዘንድ አስባለሁ።( 1ነገ 5:3-5)

በዙሪያው ሰላም በመሆኑ ምክንያት የእግዚአብሔርን ቤት ለመስራት ጊዜ፣ ገንዘብ፣ የሰዉ ሀይል የመሳሰሉትን አገኘ።  በሐጌ መጽሐፍ ላይ የእግዚአብሔር ቤት አለመሠራትና የህዝቡ በሌላና ባላስፈላጊ ነገር መጠመድ ነዉ የእግዚአብሔርን ቁጣጠያነደደውና ላለመባረካቸዉና ለመቅበዝበዛቸዉ ምክንያት የሆነዉ።  አሁንም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከተያዝንና የእግዚአብሔርን ቤት ከመስራት ከዘገየን ከሰላማችን ርቀን በብኩንነት ህይወት ዘመናችን እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ያልቃል።

 

5.3.  ህዝብ ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል 

በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፥ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።

እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ኑ፥ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ።(ት.ኢሳ 2:3-5)

 

5.4.  በከተማ ሰላም ለሰዎች ሰላም ይሆናል

በእርስዋ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና ወደ እርስዋ ላስማርክኋችሁ ከተማ ሰላምን ፈልጉ፥ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ። (ት. አር 29:7)።  ስለምንኖሮበት ህዝብና ከተማ ሰላም መጸለይና ሰላምን መፈለግ ይኖሮብናል። የአገር ሰላም የህዝብ ሰላም ነውና። 

 

5.5.  ልማት ይሆናል፤ ይፋጠናል

በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፥ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም። (ት. ኢሳ 2:4)

ለጦርነትና ለግጭት የሚዉለዉ ግዜ፣ ገንዘብ ፣ የሰዉ ሀይል ለልማት ይውላል። ጦርነት አውዳሚና አጥፊ ነዉ። ሰላም በሚኖርበት ግዜ ግን ሁለንተናዊ እድገት ይፋጠናል።

 

6. የሰላም መታጣት ዉጤት

6.1. ከተሞች ባድማ ይሆናሉ

እርሱም፡— ሂድ፥ ይህን ሕዝብ፡— መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው።  በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቍር፥ ዓይናቸውንም ጨፍን፡ አለኝ።

እኔም፡— ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው? አልሁ። እርሱም መልሶ እንዲህ አለ፡— ከተሞች የሚኖርባቸውን አጥተው እስኪፈርሱ ድረስ፥ ቤቶችም ሰው አልባ እስኪሆኑ ምድርም ፈጽሞ ባድማ ሆና እስክትቀር ድረስ፥(ት.ኢሳ 6:9-11)

ብልህ ከሌሎች ዉድቀት ሞኝ ግን ከራሱ ዉድቀት ይማራል ይባላል።  የሰሙትን እንዳያስተዉሉ፣ ያዩትን እንዳይመለከቱ ጆሮቻቸዉ ደንቁረዋል አይኖቻቸዉም ጨፍነዋል ። ፈውስንም ጨርሰዉ እንዳይቀበሉ ልባቸዉ ደንድኗል። 

ይህም የሚሆነዉ ከተሞች የሚኖርባቸውን አጥተው እስኪፈርሱ ድረስ፥ ቤቶችም ሰው አልባ እስኪሆኑ ምድርም ፈጽሞ ባድማ ሆና እስክትቀር ድረስ ነዉ።  ጦርነት የሚያስከትለዉ ውድቀት ምርምር አያስፈልገውም። የገሀዱ አለም፣ የጎረቤት አገሮች የእለት ተእለት ኑሮ ነዉ። ከተሞቻቸው ሰዉ ኑሮባቸዉ እንደማያውቅ እስኪመስሉ ወና የሆኑ ልጆቿን በሊታ የሆነች አገር የአለማችን መነጋገሪያ የሆኑና ስደተኞቻቸዉ በአለም አደባባዮች የዋሉ ቤት ይቁጠረዉ።  ይህ ወደ እኛ እንዳይመጣ ከሌሎች ተለይተን አልተከተብንም።  ይልቁን ሳንዉል ሳናድር ሰላማችንን የማስጠበቅ የቤትስራችንን በጋራና በፈቃዳችን ልንወጣ ይገባናል።

 

6.2. ሁለንተናዊ ልማት ይቋረጣል

ሰላም በህዝቦችና በሀገራት መካከል የሚናጋበት ምክንያቶች ብዙና ውስብስብ ናቸዉ። የኑሮ መወደድ፣ የደህንነት ስጋት፣ ጥቃት፣ የስልጣን ሹኩቻ፣ ዘላቂነትና አስተማማኝነት ያለዉ የምግብ አቅርቦት አጦት፣ የሌሎች አገራት ጣልቃ ገብነት እና ሌሎች የመነሻ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። 

በዚህም ምክንያት እንኳን ተስፋ የሚጣልበት የሚቀጥል ዘርፈ ብዙ ልማት፣  ለምተዉ የነበሩ መሠረተ ልማቶችና ግንባታዎች ይወድማሉ።  አገራዊና አለም አቀፋዊ ኢንቨስትመንት ይገታል። ለምቶም ከነበረ ይወድማል። በዚህ ግዜ ነው እንግዲህ የያዘን አባዜ አልለቅ ብሎን በድህነት አዙሪት ትውልድ የክብዮሽ የድህነት ኑሮዉን የሚጋፈጠዉ። ስለዚህ የሰላም መታጣት የአንድ ወገን፣ የአንድ ትውልድና የአንድ አገር ችግር ብቻ ሆኖ አይቀጥልም። የሰላም እጦት የማይነካዉ የህብረተሰብ ክፍል፣ የማይጎዳው አገር አይኖርም። ውጤቱ ድንበር ዘለል፣ ትውልድ ዘለልና ዘመን ዘለል ነዉ።

 

6.3. በአገር ውስጥ የሚፈናቀሉና ወደ ጎረቤት አገሮች የሚሰደዱ ይበዛሉ 

ሰዉ በተፈጥሮዉ የደህንነት ዋስትና ይፈልጋል። ማንም አስገድዶት ሳይሆን በሰላም መታጣት ተፈጥሮአዊ ፈተና በጦርነት ቀጠና የሚኖሩ ህዝቦች ከፊሎቹ በአገር ወስጥ ተፈናቃይነት ከፊሉም በአለም አቀፍ ስደተኝነት ከትውልድ መንደር ካደጉበት ቄዬ ለመነቀል ይገደዳሉ። በዚህ መሀል የአዉሬ እራት፣ የበረሀ ቀለብ የሚሆኑ ቁጥራቸዉ በዉል የማይታወቁ ክቡር የሰዉ ልጆች ሀምሳለ እግዚአብሔር የፈጣሪ እጅስራዎች የትዬለሌ ናቸዉ። 

ይህ ደግሞ ድንበር ዘለል፣ ዘመንና ትዉልድ ተሻጋሪ አሻራ ጥሎ ያልፋል። የአገርንም ሉአላዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። ከባሰም ለመኖር ምቹ ካልሆኑ አገራት ተርታ ያስመድባል። አሻራዉ በሰላም እጦት ለተጎዱት አገራትና ዜጎች ብቻ ሳይሆን በቀጣናዉ ላሉ የጎረቤት አገራትም ጭምር ይሆናል።

 

7. ሰላምን ለማግኘና ለማስጠበቅ የተሰጡ  መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክሮች

 

 • ሰላምን መሻትና መከታተል

ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤  የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።  በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? (1ጴጥ 3:8-13)

 

 • ታራቂ፣ ገርና እሺ ባይ መሆን

ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም።  ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን?

ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም።  ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ።

ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ።

ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና።  ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።(ያእቆብ መልእክት 3:17)

 

 • መልካም ዘርን መዝራት

ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ?  አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ።  ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን እሻ ተከተላትም።

የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና።   መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው።( መዝሙር 34:12-16)

 

ታህሳስ 1, 2013 ዓ.ም

ቤተልሔም አበራ

©ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ ኢትዮጵያ። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።