መጣጥፎች

የህይወት ምስክርነትህ


የአንተ ታሪክ የእርሱ ታሪክ ነው

ታሪካችንን (ምስክርነታችንን) በተናገርን ጊዜ ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብርን እያመጣን ነው፤ እርሱም በዚህ ይደሰታል።

ታሪክህ የቱንም ያህል "አስደናቂ " ወይም "ተራ" መስሎ ቢታይህም ስለ እግዚአብሔር ባህርይ የሚተርክ ነው። እግዚአብሔር ከሃጢአትና ከሞት በክርስቶስ በኩል አድኖህ ህይወትህን እንዴት እንደለወጠው የዓይን እማኝ የሆንክበት ምስክርነትህ ነው ።

ታሪካችንን ለሌሎች ሰዎች ስናጋራ እግዚአብሔር ማን እንደሆነና ምን ማድረግ እንደሚችል እንዲያውቁ እየረዳናቸው ነው፡፡

ተዘጋጅ

በመገበያያ ቦታ ለክፍያ ተሰልፈህ ቢሆን፣ ከቤተሰብ አባልህ ጋር ተቀምጠህ ቢሆን ወይም ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ቆመህ ቢሆን መፅሐፍ ቅዱስ በክርስቶስ በኩል ስላገኘነው ተስፋ በትህትናና በአክብሮት ለሌሎች ለማጋራት " ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ" ይለናል (1ኛ ጴጥሮስ 3፡ 15-16)። 

አንዳንድ ጊዜ ታሪኩ የራሳችን ስለሆነ ለመናገር ምንም ዝግጅት አያስፈልገንም ብለን እናስባለን። ምክኒያቱም ታሪኩ ሲፈፀም ስለነበርንና አሁንም እየኖርነው ስለሆነ።

ይህ ሆኖ ሳለ ግን ታሪካችንን ስናጋራ ልንፈራ፣ ከዋናው ሃሳብ ልንወጣ ወይም የምንናገረው ምስክርነት ምን እንደሆነ ልንረሳ እንችላለን፤ ይህ ደግሞ የሚሰሙን ሰዎች ግራ እንዲጋቡና እንዲምታቱ ያደርጋቸዋል። ለዚህ ነው ትንሽ ዝግጅትና ልምምድ በጣም አስፈላጊ የሆነው።

ታሪክህን ሰብሰብ አድርገው

ታሪክህን እንዴት ስብስብ ማድረግ እንደምትችል አንድ በአንድ እንመልከት፡፡ ታሪክህ አምስት መሠረታዊ አካላት አሉት፦ መክፈቻ፣ ከክርስቶስ በፊት የነበረህ ህይወት፣ ወደ ክርስቶስ እንዴት እንደመጣህ፣ ወደ ክርስቶስ ከመጣህ በኋላ ያለህ ህይወት እና መዝጊያ ናቸው፡፡

  1. መክፈቻ፦ የታሪክህ ጭብጥ ሊሆን የሚችል አንድ ሃሳብ ለይ፡፡ ህይወትህ ይሽከረከር የነበረው በምን ዙሪያ ነው (ለምሳሌ በግንኙነቶች፣ በዝናህ ላይ፣ በገንዘብ)? እግዚአብሔር በየትኛው በኩል አገኘህ? የህይወትህ ማዕከል የነበረው ነገር በአንተ ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ እንደነበረው በአጭሩ አብራራ።

  2. ከክርስቶስ በፊት የነበረህ ህይወት፦ ወደ ክርስቶስ ከመምጣትህ በፊት ህይወትህ ምን ይመስል እንደነበር ተናገር። ያለፈው የሃጢአት ተግዳሮትህ ላይ ብዙ ሰዓት አታጥፋ፤ ወይም ስለዚያ ህይወትህ በኩራት አታውራ። ከታሪክህ ጭብጥ ጋር የሚሄድ እንዲሆን - ማለትም ክርስቶስ ምን ያህል ያስፈልግህ እንደነበር ለማብራራት ዋና ዋናውን ብቻ ተናገር።

  3. ወደ ክርስቶስ እንዴት እንደመጣህ፦ ለምንና እንዴት ክርስቲያን እንደሆንክ ዋናውን ጭብጥ ተናገር። እየነገርከው ያለኸው ወይም ሌላ በድንገት የሰማህ ሰው እንዴት ክርስቲያን መሆን እንደሚችል መረዳት በሚችልበት መንገድ ሃሳብህን አስተላልፍ። እየሰሙህ ያሉት ሰዎች በዚያ ቅፅበት ለመወሰን ዝግጁ ባይሆኑም እግዚአብሔር በአንተ ታሪክና ስለ ወንጌል በነገርካቸው እውነት ወደፊት ወደ ራሱ ሊያመጣቸው ይችላል።

  4. ወደ ክርስቶስ ከመጣህ በኋላ ያለህ ህይወት፦ ከታሪክህ ጭብጥ ጋር የሚገናኙ ክርስቶስ በህይወትህ ያደረጋቸውን ለውጦች አካፍል ። በውጪ በሚታየው ፀባይህ ላይ ሳይሆን በውስጥ ባህሪህ፣ በአመለካከትህና ዕይታህ ላይ በመጡት ለውጦች ላይ አተኩር፡፡ ከእውነታውም አትሽሽ፡፡ ምንም ክርስቲያኖች ብንሆን ተግዳሮቶች ግን አሉብን። ህይወት ከፍፁምነት የራቀች ብትሆንም፣ በአንተ ህይወት አሁን የተለየ የምትለው ነገር ምንድነው?

  5. መዝጊያ፦ ታሪክህን በሚያጠቃልል እና ከዋናው የታሪክህ ጭብጥ ጋር በሚገናኝ ንግግር አገባድ። ከፈለግክም ከታሪክህ ጋር በሚገናኝ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሃሳብህን ቋጭ።

ጠቃሚ ምክሮች

  • ታሪክህን ከመፃፍህ ወይም ከማጋራትህ በፊት ፀልይ።

  • የምትፅፍ ከሆነ የምትፅፈው እንደምትናገርበት አግባብ ይሁን፡፡

  • ከተገቢው በላይ አሉታዊም አዎንታዊ አትሁን። በንግግርህ ታማኝ ሁን።

  • የቤተ ክርስቲያንን፣ የሃይማኖት ወገንን ወይም የድርጅት ስምን አታንሳ ወይም አትተች።

  • ስለምትግራቸው ሰዎች አስብ። እጅግ ሃይማታዊ ቃላትን አትጠቀም።

  • ታሪክህን በአጭሩ አቅርብ። ከሦስት እስከ አምስት ደቂቃ ውስጥ ታሪክህን ለመናገር ሞክር።

  • ከአንተ ጋር እስኪዋሃድ ድረስ ታሪክህን ማጋራትን ተለማመድ፡፡


አሁን ታሪክህን እንዴት ማጋራት እንዳለብህ ስለተማርክ "የአንተ ታሪክ የእግዚአብሔር ታሪክ ነው፦ ምስክርነትህን አዘጋጅ" በሚለው መመሪያ ላይ ታሪክህን ፃፍ፡፡

©ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ ኢትዮጵያ። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።