ደቀመዛሙርትን ማፍራት

የቡድን ውይይትን መምራት

የቡድን ውይይት በሚገባ ከሚጫወቱት ማራኪ የእጅ ኳስ ጨዋታ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እንደ መሪ፣ ጥሩ ጥያቄ በመጠየቅ ኳሱን ትጀምራለህ። ቀጣዩም ሰው በቡድኑ ውስጥ ለሚገኝ ሌላ ተጫዋች ኳሱን አስተካክሎ በማቀበል መልስ ይሰጣል። 

አስደሳች የእጅ ኳስ ለመጫወት ልምምድ፣ ዝግጅትና በትጋት መስራትን እንደሚጠይቅ ሁሉ፣ ጥሩ የሚባሉ የቡድን ውይይቶችም እንዲሁ ናቸው። 

በቡድንህ ውስጥ ጥሩ የሆነ ውይይትን ለመምራት እንድትችል ጥያቄ መጠየቅና በሚገባ ማዳመጥ የምትችልባቸው 5 የተለያዩ መንገዶች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል። 

የመግቢያ ጥያቄዎች

ለጥናትህ ወይም ለውይይቱ መነሻ መሆን ከሚችሉ ጥሩ መንገዶች ውስጥ አንዱ ልታነበው ወዳለኸው የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ሃሳብ ሊመራ የሚችል ሰፋ ያለ ጥያቄን ማንሳት ነው።

እነዚህ ጥያቄዎች የማፍታቻ ሃሳቦች ከተሰነዘሩ በኋላና ወደ ዋናው የመፅሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመግባትህ በፊት የሚመጡ ናቸው። እግዚአብሔር ለህይወታችን ያለውን አስፈላጊነት በምታነበው ክፍል ውስጥ በጉልህ ከተጠቀሰው ሃሳብ ጋር ለማዛመድ ይረዳሉ፡፡

ጥያቄ፡ በህይወትህ ብቁ እንዳልሆንክ የተሰማህን ወቅት ግለፅ፡፡ ( ይህ ጥያቄ ስለ ፀጋና ይቅርታ ለማጥናት መሪ ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡)

ጥያቄ፡ በልጅነት እድገትህ ጀግናዬ ትለው የነበረውን ሰው ስም ተናገር፡፡ እንደ እርሱ/እርሷ መሆን እንድትፈልግ ያደረገህ ምንድነው? (በዚህ ጥያቄ ላይ በመመስረት ጳውሎስ አንባቢዎቹ "እግዚአብሔርን እንዲመስሉ" ያበረታታበትን ኤፌሶን ምዕራፍ 5ን ወይም በ1ኛ ጤሞቶዎስ ምዕራፍ 4 መሠረት "አርኣያ ስለመሆን" ማጥናት ይቻላል።)

የአሰሳ ጥያቄዎች

የመግቢያውን ጥያቄ ከጠየቅክና ክፍሉን ከከለስህ በኋላ የቡድንህ አባላት እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ ምን እየተናገረ እንደሆነ እንዲረዱ ጥያቄዎችን ትጠይቃለህ። የክፍሉ ዋና ሃሳብ ላይ ለመድረስ እንዲቻል እነዚህ ጥያቄዎች በክፍሉ ላይ ያተኮሩና ለተጨማሪ ጥያቄ በር የሚከፍቱ እንዲሆኑ በማድረግ በሚከተሉት ላይ የሚያተኩሩ መሆን አለባቸው፡

  • ክፍሉ ምን ይላል? (የዳሰሳ/የምልከታ ጥያቄዎች)

  • የክፍሉ ትርጉም ምንድነው? (የትርጓሜ ጥያቄዎች)

  • የክፍሉ ጥቅም ምንድነው? (የክፍሉ ጠቀሜታ ጥያቄዎች)

ወደፊት ከመሄድህ በፊት የቡድንህ አባላት የክፍሉን ዋና ሃሳብ መጨበጥ እንዲችሉ እርዳቸው። የክፍሉን ዋና ጭብጥ ወይም ዋና ነጥብ ማየት እንዲችሉ ተያያዥ ጥያቄን ጠይቅ።

ጥያቄበኤፌሶን 2፡1-10 መሠረት ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች ስለ ፀጋ እንዲረዱ የፈለገው ምን ይመስልሃል? 

ልባዊ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች

የቡድን መፅሐፍ ቅዱስ ጥናትህ መንፈሳዊ ስብራትን (ከኢየሱስ ጋር ካለ ህብረት ውጪ ለመሆን የሚፈልግን ልብ) የሚያጋልጥ ከሆነና ኢየሱስ የዚህ ስብራት ብቸኛ መፍትሄ እንደሆነ ማሳየት የሚችል ከሆነ እጅግ ውጤታማ የቡድን ጥናት ነው ማለት ነው፡፡ 

በቅድሚያ ቡድንህ በክፍሉ ላይ የተጠቀሰውን ሃሳብ በተግባር መኖር ምን እንደሚመስል እንዲረዳ የሚያግዙ ጥያቄዎችን ጠይቅ። 

ጥያቄ፡ የክርስቶስ የእጁ ስራዎች ተብለን ተጠርተናል(ኤፌሶን 2፡10)፡፡ ይህ ሃሳብ ክርስቶስን በሚከተል ሰው ህይወት ውስጥ እንዴት ይታያል? 

ቀጥሎም ለህይወታችን አዳኝ እንደሚያስፈልገን የሚያሳዩና ልብ ምን ያህል ከክርስቶስ የተነጠለ ህይወትን ለመኖር እንደሚፈልግ የሚያገልጡ የተወሰኑ ጥያቄዎችን ጠይቅ። 

ጥያቄ፡ የምንኖርበት ባህል መሆን የምንፈልገውን የትኛውንም ነገር መሆን እንደምንችል ይነግረናል። ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ከእግዚአብሔር ጋር በምታደርገው የህይወት ጉዞ ውስጥ እንዴት ቀስ በቀስ ሊገባ ይችላል? 

ከዚያም ቡድንህን ለመንፈሳዊ ስብራት ብቸኛ መፍትሄ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ የሚመሩ የተወሰኑ ጥያቄዎችን ጠይቅ። 

ጥያቄ፡ አብዛኛውን ጊዜ የወደፊት ህይወታችን ምን እንዳዘለ ማወቅና መቆጣጠር እንፈልጋለን፤ ለወደፊት ህይወታችን ኢየሱስን ማመን የሚሳነን ለምንድነው?

ጥያቄ፡ ኢየሱስ ስለ አንተ ግድ እንደሚለውና ለአንተ የሚያስበው ሃሳብ እጅግ በጎ እንደሆነ ከልብህ ብታምን ህይወትህ ምን ያህል የተለየ ሊሆን ይችላል?

የእነዚህ ጥያቄዎች ግብ የቡድንህ አባላት ባህሪያቸውን በግል ጥረታቸው ለመቀየር ካላቸው ተፈጥሮአዊ ፍላጎት በማውጣት የህይወትና የዕድገት ምንጭ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ መምራት ነው፡፡

ህብረትንና ግንኙነትን የሚያጎለብቱ ጥያቄዎች

የመግቢያ ጥያቄዎች፣ የአሰሳ ጥያቄዎች እና የልብ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች የክፍሉን ሃሳብ የሚገልጡ፣ የሃጢአታችንን ስር መሠረት የሚያሳዩ እና ለኢየሱስ መስጠት የሚገባንን ምላሽ የሚጠቁሙ ሲሆኑ እጅግ አንገብጋቢ ጥያቄዎችም ናቸው፡፡

ልብ ላይ የተመረኮዙ ጥያቄዎች ላይ የሚያተኩረው የመፅሐፍ ቅዱስ ጥናትህ በእውነተኝነት፣ በታማኝነትና በህብረት ማድግ አለበት። ነገር ግን ቡድኑን ለውይይት የሚያነሳሱና ማህበራዊ መስተጋብሩን የሚያጎለብቱ ጥያቄዎችንም ማሰብ ጠቃሚ ነገር ነው። 

እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ጥቅም አልባ አይደሉም። የመጀመሪያው ግብህ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር እንዲገናኙ ማድረግ ቢሆንም፣ እርስ በርሳቸውም እንዲገናኙ ማድረግም ይኖርብሃል፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር ያለው ህብረትም ከክርስቶስ ጋር ወደ መገናኘት የሚያመራ ነው፡፡ 

ጥያቄ፡ ዛሬ ባነበብነው ክፍል ላይ ለህይወታችን በጣም አበረታች የሆነው ሃሳብ የትኛው ነው? ተግዳሮት የሚሆነውስ? ለምን?

የተሻለ አዳማጭ መሆን

ጥሩ የሚባሉ ውይይቶችን በማድረግ ሂደት ውስጥ ጥያቄዎችን መጠየቅ የውይይቱ ግማሽ አካል ብቻ ነው፡፡ ማዳመጥ ደግሞ ሌላኛው አካል ነው።

በሚገባ ስታዳምጥ በቡድንህ ለሚገኙ ሌሎች አባላት ሃሳብ ቦታ እንደምትሰጥ እያሳየህ ነው። ይህ ደግሞ አግባብነት ያላቸውን ጥያቄዎች እንድትጠይቅና ቡድንህም በውይይቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ያደርጋል። 

የቡድህ አባላት ሃሳባቸውን ሲያጋሩ፡

  • ሁኔታውን ከእነርሱ ዕይታ አንፃር ለመመልከት ሞክር፡፡

  • ሃሳባቸውን በማጋራታቸውና ጥያቄዎችን በመጠየቃቸው በማመስገን አበረታታቸው፡፡

  • በንቃት አዳምጥ። የተናገሩት ሃሳብ ግልፅ ካልሆነልህ ሃሳባቸውን በራስህ አባባል ድገመውና በትክክል ተረድተኸው እንደሆነ መልስህ ጠይቅ

  • በመላ "ተክለ ሰውነትህ" አዳምጥ። ከሚናገረው ሰው ጋር የዓይን ለዓይን ግንኙነት አድርግ፤ የአቀማመጥ ሁኔታህም ላይ ትኩረት አድርግ። አቀማመጥህ (ለምሳሌ እጅህን ደረትህ ላይ ማጣመርና በጀርባህ ወንበርህ ላይ መተኛት) ወይም ለቀረበው ሃሳብ ምላሽ የምትሰጥበት መንገድ ለሌሎች አባላት ሃሳብ ቦታ እንደሌለህ ሊያመለክት ይችላል።

 

©ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ ኢትዮጵያ። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።