እግዚአብሔርን ማወቅ

ሥላሴን መረዳት

ጆን ፓይፐር

 

የሥላሴ አስተምህሮ የክርስትና እምነት መሠረት ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ማንነት ለማወቅ፣ እርሱ ከእኛ ጋር በምን መልኩ ህብረት እንደሚያደርግና እኛም ከእርሱ ጋር እንዴት ህብረት ማድረግ እንዳለብን ለመረዳት እጅግ አስፈላጊ አስተምህሮ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ከበድ ያሉ ጥያቄዎች ያሉበትም ትምህርት ነው። እግዚአብሔር እንዴት በአንድ ጊዜ አንድና ሦስት ይሆናል? ትምህርተ ሥላሴ እርስ በእርሱ ይቃረናል? ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ወደ እግዚአብሔር እንደፀለየ በወንጌላት ላይ ለምን ተገለፀ? ሥላሴን ( ወይም የትኛውንም ሌላ ነገር ቢሆን) ሙሉ በሙሉ መረዳት ባንችልም ከላይ የተጠቀሱትን ዓይነት ጥያቄዎች በመመለስ እግዚአብሔር ሦስትና አንድ ነው ማለት ምን እንደሆነ ጠንካራ ጭብጥ ይኖረናል።

እግዚአብሔር ሥሉስ አምላክ ነው ማለት ምን ማለት ነው?

የሥላሴ አስተምህሮ ማለት እግዚአብሔር ሦስት የተለያዩ አካላት ማለትም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የሆነ አንድ አምላክ ነው ማለት ነው። በሌላ አገላለፅ እግዚአብሔር በማንነት፣ በመለኮትና በህልውና አንድ ሲሆን በአካል ግን ሦስት ነው ማለት ነው፡፡ ይህ አተረጓጐም ሦስት ጠቃሚ እውነቶችን ያዘለ ነው፦ (1) አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሦስት የተለያዩ አካላት ናቸው፥ (2) እያንዳንዱ የሥላሴ አካል ሙሉ አምላክ ነው፥ (3) እግዚአብሔር አንድ አምላክ ነው።

አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሦስት አካላት ናቸው

መፅሐፍ ቅዱስ አብ አምላክ እንደሆነ (ፊልጵስዩስ 1፡2)፣ ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ (ቲቶ 2፡13) ፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ እንደሆነ (ሐዋርያት ሥራ 5፡3-4) ይናገራል። እነዚህ ክፍሎች የሚያሳዩት አንድ እግዚአብሔርን የምንረዳበት ሦስት የተለያዩ መንገዶች ወይም ስለ አንድ እግዚአብሔር ሦስት የተለያዩ ገጽታዎች ነውን?

መልሱ አይደለም መሆን አለበት ምክኒያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያመለክተው  አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሦስት አካላት እንደሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ በዮሐንስ 3:16 መሠረት አብ ወልድን ወደ ዓለም እንደላከው ስለተገለፀ ከወልድ ጋር አንድ አካል ሊሆን አይችልም። በተጨማሪም በዮሐንስ ወንጌል 16፡ 1ዐ መሠረት ወልድ ወደ አብ ከተመለሰ በኋላ አብና ወልድ መንፈስ ቅዱስን ወደ ዓለም ይልካሉ (የሐንስ 14:26፣ ሐዋርያት ስራ 2:33)፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና ወልድ ሌላ ሦስተኛ አካል ነው ማለት ነው።

በማርቆስ 1፡1ዐ-11 ላይ እንደተጠቀሰው ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ከውሃው ሲወጣ እግዚአብሔር ከሰማይ በድምፅ ሲናገርና መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል ከሰማይ ሲወርድ እንመለከታለን፡፡ በዮሐንስ 1፡1 ላይ ኢየሱስ እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነና በተመሳሳይ ጊዜም "ከእግዚአብሔር ጋር" እንደነበር በማመልከት ኢየሱስ ከአብ የተለየ አካል እንደሆነ ያሳያል (1:18ን በተጨማሪ ተመልከት)። በዮሐንስ 16፡13-15 ላይ በሥላሴ መሃል ጥብቅ የሆነ አንድነት እንደተጠበቀ ሆኖ መንፈስ ቅዱስ እንደአብና ወልድ የራሱ አካል እንዳለውም ተጠቅሷል። አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሦስት አካል ናቸው ማለት በሌላ አባባል አብ ወልድ አይደለም፤ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስ አብ አይደለም  ማለት ነው። ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው፤ ነገር ግን አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ አይደለም። መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፤ ነገር ግን አብ ወይም ወልድ አይደለም። ሦስት አካል ናቸው እንጂ አንድ እግዚአብሔርን የምናይባቸው ሦስት መንገዶች አይደሉም።

ሥላሴ ሦስት አካል መሆኑ እያንዳንዱ የራሱ የሆነ ሃልዎት ያለው እንደሆነ ያሳያል፡፡ ስለዚህም እርስ በርስ ግንኙነት የሚያደርጉትም በዚህ መሠረት ነው፦ አብ ራሱን "እኔ" (1ኛ መደብ) ብሎ ሲጠራ ወልድን ወይም መንፈስ ቅዱስን ደግሞ "አንተ" (2ኛ መደብ) ብሎ ይጠራል። በተመሳሳይም መንገድ ወልድ ራሱን "እኔ" ብሎ ሲጠራ አብን ወይም መንፈስ ቅዱስን "አንተ" ብሎ ይጠራል። 

ብዙ ጊዜ "ኢየሱስ አምላክ ከሆነ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት መፀለይ የነበረበት ወደ ራሱ ነው'' የሚል ተቃውሞ ይስተዋላል። ነገር ግን ከላይ የተመለከትነው እውነት ለዚህ ተቃውሞ በቂ መልስ ነው። ኢየሱስና አብ አምላክ ቢሆኑም ሁለት የተለያዩ አካላት ደግሞ ናቸው። ስለዚህ ኢየሱስ ወደ አብ እንጂ ወደ ራሱ አልፀለየም። እንደውም በአብና በወልድ መሃል ያለው ቀጣይነት ያለው ንግግር (ማቴዎስ 3፡17፣ 17፡5፣ ዮሐንስ 5፡19፣ 11፡41-42፣ 17: ከ1ጀምሮ ) ሁለት የራሳቸው ሃልዎት ያላቸው አካላት ለመሆናቸው በቂ ማስረጃ ነው። 

አንዳንድ ጊዜ በአብና በወልድ ላይ ትኩረት እናደርግና መንፈስ ቅዱስን ግን እንዘነጋለን። አንዳንዴ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ሃልዎት እንዳለው አካል ሳይሆን እንደ "ሃይል" ተደርጐ ይወሰዳል። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ሃይል ሳይሆን የራሱ ሃልዎት ያለው አካል ነው (ዮሐንስ 14:26፣ 16፡7-15 እና ሐዋርያት ስራ 8:16 ን ተመልከት)። መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ አካል መሆኑንና ዝም ብሎ ሃይል አለመሆኑን (ልክ የመሬት ስበት ሃይል እንደምንለው) የሚናገር በመሆኑ (ዕብራውያን 3፡7)፣ በምክኒያታዊነቱ (ሐዋርያት ስራ 15፡ 28) ፣ ማሰብና መረዳት በመቻሉ (1ኛ ቆሮንቶስ 2፡10-11)፣ ፈቃድ ያለው በመሆኑ (1ኛ ቆሮንቶስ 12፡11)፣ ስሜት ያለው በመሆኑ (ኤፌሶን 4፡30) እና የግል ህብረትን የሚሰጠን በመሆኑ (2ኛ ቆሮንቶስ 13፡14) በእነዚህ ማየት ይቻላል። እነዚህ ባህሪያት ራሱን የቻለ ማንነት ያለው አካል መገለጫዎች ናቸው። ከእነዚህ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በተጨማሪ ከላይ ያሉት ክፍሎችም መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የሚለይ ሌላ አካል መሆኑን በግልፅ ያሳዩናል። ስለዚህም እነዚህ ሦስት የሥላሴ አካላት እንጂ የአንድ እግዚአብሔር ሦስት የተለያዩ ገጽታዎች አይደሉም፡፡ 

በሥላሴ ዙሪያ ሰዎች የሚሳሳቱት ሌላው አደገኛ ስህተት ደግሞ አብ ወልድ ሆነ፤ ቀጥሎ ወልድ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ሆነ የሚል ነው፡፡ ከዚህ ዕይታ በተቃርኖ ግን ከላይ ያየናቸው ክፍሎች እግዚአብሔር ሦስት አካል መሆኑን ያሳዩናል። በሥላሴ ውስጥ ያለ የትኛውም አካል ያልነበረበት ጊዜ የለም። ሦስቱም አካላት ዘላለማዊ ናቸው።

ሥላሴ ሦስት አካል ቢሆንም አንዱ የሥላሴ አካል ግን ከሌላው ያንሳል ማለት አይደለም። በአንፃሩ በባህርይ ሁሉም አቻ ናቸው። በሃይል፣ በፍቅር፣ በምህረት፣ በፍርድ፣ በቅድስና፣ በዕውቀት እና በሌሎች ባህሪያት ሦስቱም እኩል ናቸው። 

እያንዳንዱ የሥላሴ አካል ምሉዕ አምላክ ነው

እግዚአብሔር ሦስት አካል ነው ካልን እያንዳንዱ አካል የሥላሴ ሲሶ (አንድ- ሦስተኛ) ነው ማለት ነው? ሥላሴ ማለት እግዚአብሔር በሦስት ይከፈላል ማለት ነው?

ትምህርተ ሥላሴ እግዚአብሔርን በሦስት ቦታ አይከፋፍልም፡፡ እንደ መፅሐፍ ቅዱስ ግልፅ አስተምህሮ እያንዳንዱ የሥላሴ አካል ራሱ መቶ በመቶ አምላክ ነው።አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሦስቱም ምሉዕ አምላክ ናቸው ። ለምሳሌ በቆላስያስ 2፡9 ላይ ስለ ክርስቶስ ሲናገር "የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በእርሱ ይኖራልና፤" ይላል። እግዚአብሔርን "ኬክ" ሦስት ቦታ ሲቆረጥ እያንዳንዱ ቁራጭ አንዱን የሥላሴ አካል ይወክላል በሚለው ምሳሌ መመሰል የለብንም። ይህ ምሳሌ እያንዳንዱ የሥላሴ አካል ምሉዕ ያልሆነና (የሙሉው ክፋይ እንደሆነና) በዚህም ምክኒያት አምላክ /እግዚአብሔር/ እንዳልሆነ የሚያመለክት ነው። እውነታው ግን "የእያንዳንዱ የሥላሴ አካል ማንነት ከእግዚአብሔር ሙሉ ማንነት ጋር እኩል ነው፡፡" የመለኮት ባህርይ በሦስቱ አካላት መሃል የተከፋፈለ ሳይሆን በእያንዳንዱ የሥላሴ አካል ውስጥ ያለምንም "መከፋፈል" በሙላት የሚገኝ ነው። 

ስለዚህ ወልድ የእግዚአብሔር ሲሶ (አንድ ሦስተኛ) ሳይሆን እርሱ ምሉዕ የሆነ እግዚአብሔር ነው። አብ የእግዚአብሔር ሲሶ (አንድ ሦስተኛ) ሳይሆን እርሱ ምሉዕ የሆነ እግዚአብሔር ነው። መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ። ዋይን ግሩደም እንደፃፈው፦ "ስለ አብ፣ ስለ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በአንድነት ስናወራ ስለ አብ ብቻ፣ ስለ ወልድ ብቻ ወይም ስለ መንፈስ ቅዱስ ብቻ ከምናወራው የበለጠ ማንነት እያወራን አይደለም፡፡"  

እግዚአብሔር አንድ ነው

እያንዳንዱ የሥላሴ አካል ልዩ ከሆነና በራሱ ምሉዕ አምላክ ከሆነ እግዚአብሔር ከአንድ በላይ ነው ብለን መደምደም አለብን? መፅሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አንድ ነው ስለሚል እንደዚያ ብለን መደምደም አንችልም፦ " ጻድቅና አዳኝ የሆነ አምላክ፣ ከእኔ በቀር ማንም የለም፤ ከእኔ ሌላ አምላክ የለም።  እናንት የምድር ዳርቻ ሁሉ፣ እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና፤ ትድኑ ዘንድ ወደ እኔ ተመለሱ'' (ኢሳያስ 45፡21-22፣ በተጨማሪም 44፡6-8፣ ዘፀአት 15:11፣ ዘዳግም 4፡35፣ 6:4-5፣ 32:39፣ 1ኛ ሳሙኤል 2፡2 ፣ 1ኛ ነገስት 8፡60 ተመልከት፡፡) 

አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በአካል ሦስት መሆናቸውን፣ እያንዳንዳቸውም ምሉዕ መሆናቸውንና እግዚአብሔር አምላክ ግን አንድ መሆኑን ከተመለከትን በኋላ ሁሉም የሥላሴ አካላት ያው አንዱ እግዚአብሔር እንደሆኑ መደምደም አለብን። በሌላ አገላለፅ እግዚአብሔር በሦስት የተለያየ አካል የሚኖር አንድ አምላክ ነው ማለት ነው። 

ይህንን ሃሳብ በአንድ አጠቃሎ የያዘ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ቢኖር ማቴዎስ 28፡ 19 ነው፦ "ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።" በመጀመሪያ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በሦስት አካል ተገልፀዋል፡፡ የምናጠምቀው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው። ሁለተኛ ሦስቱም በአንድ ደረጃ ስለተቀመጡ እያንዳንዳቸው አምላክ ናቸው ማለት ነው። በርግጥ ኢየሱስ ይህንን ትዕዛዝ ሲሰጥ በሌላ ፍጡር በሆነ አካል ስም እንድናጠምቅ ሊፈቅድ ይችል ነበር? በርግጥ እንደዚያ አያደርግም። ስለዚህ በስሙ የምንጠመቀው እያንዳንዱ የሥላሴ አካል አምላክ ነው ማለት ነው፡፡ ሦስተኛ ሥላሴ ሦስት የተለያየ አካል ቢሆንም የምንጠመቅበት ስም የተገለፀው በነጠላ ገላጭ ቃል እንጂ ብዙ አመልካች ቃል አይደለም። በአካል ሦስት ቢሆኑም ያላቸው ስም ግን አንድ ነው፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው በማንነት አንድ ከሆኑ ብቻ ነው።

ትምህርተ ሥላሴ እርስ በእርሱ የሚቃረን ነው?

ይህ ሃሳብ ከላይ የጠቀስኩትንና የሥላሴን ምንነት ያብራራሁበትን፦ እግዚአብሔር በማንነት አንድ ነው፤በአካል ግን ሦስት ነው የሚለውን ትርጉም በይበልጥ እንድንመረምር በር ይከፍትልናል። ይህ አተረጓጐም ሦስት አምላክ እንደሌለና ትምህርተ ሥላሴ ደግሞ እርስ በርሱ ተቃርኖ የሌለበት መሆኑን ያሳየናል።

አንድ ነገር እርስ በርሱ የሚቃረን እንዲሆን የኢ-ተቃርኖን ህግ መጣስ ይኖርበታል። ህጉ እንደሚለው "ሀ" በተመሳሳይ ጊዜና በተመሳሳይ ግንኙነት ውስጥ ራሱን ("ሀ" መሆንን) እና ከ"ሀ" ውጪ መሆን ("ሀ" አለመሆንን) አይችልም። በሌላ አገላለፅ አንድ የተናገርከው ነገር አንድ ጊዜ ልክ ነው ብለህ ካፀደቅክ በኋላ በተመሳሳይ ጊዜ ልክ አይደለም ብለህ ከካድክ ንግግርህ ተቃርኖ አለበት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ጨረቃ ሙሉ በሙሉ የተሰራችው ከዐይብ ነው ካልኩ በኋላ መልሼ አይ ልክ አይደለም ጨረቃ ሙሉ በሙሉ ከዐይብ አይደለም የተሰራችው ብል ራሴን እየተቃረንኩ ነው ማለት ነው።

ሌሎች ንግግሮች ደግሞ ከላይ ከላይ ስናያቸው እርስ በርስ የሚቃረኑ የሚመስሉ፤ ነገር ግን በደንብ ካየናቸው እርስ በርስ የማይቃረኑ ደግሞ አሉ፡፡ የነገረ መለኮት አዋቂው አር. ሲ. ስፕሮውል ይህንን ሃሳብ ለማብራራት፦"ይህ ጊዜ ከጊዜያት ሁሉ ምርጡ ነበር፤ ደግሞም ከጊዜያት ሁሉ መጥፎው ነበር" የሚለውን የዲክንስን ታዋቂ ፅሑፍ ይጠቀማል። በርግጥም ዲክንስ ጊዜው መጥፎና ምርጥ ነው ያለው በተመሳሳይ አግባብ ከሆነ ተቃርኖ አለበት። ነገር ግን ለማለት የፈለገው ጊዜውን በአንድ በኩል ስናየው በጣም ምርጥ ነው፤ በሌላ በኩል ስናየው ግን በጣም መጥፎ ነው ማለቱ ነው። 

ይህንን ፅንሰ ሃሳብ ወደ ትምህርተ ሥላሴ ስንወስደው እግዚአብሔር ሦስትም ነው አንድም ነው ስንል እርስ በርሱ አይቃረንም ምክኒያቱም ሦስት እና አንድ ነው የምንለው በተመሳሳይ አግባብ አይደለም። ሦስት የሆነው አንድ ከሆነበት በተለየ አግባብ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አንድ ነው ብለን መልሰን እየካድን ሦስት ነው እያልን በሚያታልል ምላስ እያወራን አይደለም። እግዚአብሔር በአንድ ጊዜ አንድና ሦስት ነው፤ ነገር ግን በተመሳሳይ አግባብ አይደለም የሚለውን ሃሳብ መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ 

እግዚአብሔር አንድ የሆነው እንዴት ነው? በማንነቱ አንድ ነው። እግዚአብሔር ሦስት የሆነው እንዴት ነው? በአካል ሦስት ነው፡፡ ማንነት እና አካል ተመሳሳይ ነገሮች አይደሉም። እግዚአብሔር በአንድ አግባብ (በማንነት) አንድ ነው፤ በሌላ አግባብ (በአካል) ግን ሦስት ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አንድ የሆነበት አግባብ ሦስት ከሆነበት ስለሚለይ ትምህርተ ሥላሴ እርስ በርሱ የሚቃረን አይደለም። እርስ በርሱ የሚቃረነው እግዚአብሔር አንድና ሦስት የሆነበት አግባብ ተመሳሳይ ነው ካልን ብቻ ነው፡፡

እስቲ እግዚአብሔር በማንነት አንድ በአካል ግን ሦስት ነው የሚለው ሃሳብ እርስ በርሱ የሚቃረን አይደለም የሚለውን ሃሳብ ጠለቅ ብለን እንመልከት። እግዚአብሔር ሦስት ሳይሆን አንድ መሆኑን እንዴት ያሳየናል? መልሱ ቀላል ነው፦

ሦስቱም የሥላሴ አካል አንድ አምላክ ነው፤ ምክኒያቱም ከላይ እንዳየነው በማንነት አንድ ስለሆኑ፡፡ ማንነት አንድ ነገር "ሁል ጊዜ ሆኖ የሚገኝበት አግባብ'' / ህላዌ / ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በህላዌነቱ አንድ እንጂ ሦስት አይደለም። ይህ ዕይታ ሦስቱም የሥላሴ አካል አንድ መሆኑን በግልፅ ያሳየናል። ይህንን ካልተቀበልን ግን የእግዚአብሔርን አንድነት እየካድንንና ከአንድ በላይ አምላክ አለ እያልን ነው፡፡

እስካሁን የተመለከትነው ሁሉ ስለ ሥላሴ መሠረታዊ መረዳት እንዲኖረን የሚያደርግ ነው። ነገር ግን ከዚህም ጠልቀን መግባት እንችላለን። ማንነትና አካል የሚሉትን ሃሳቦች በሚገባ ከተረዳን፣ እንዴት እንደሚለያዩና እንዴት እንደሚገናኙ ካወቅን ስለ ሥላሴ የተሻለመረዳትን እናገኛለን። 

ማንነት እና አካል

ማንነት

ማንነት ማለት ምን ማለት ነው? ከዚህ ቀደም እንዳልኩት ማንነት ማለት "ሆኖ መገኘት" /ህላዌ / ነው፡፡ የእግዚአብሔር ማንነት ሆኖ የሚገኝበት ሁኔታ ነው። የበለጠ ግልፅ ለመሆን፣ ማንነትህ አንተነትህ ነው። ማንነትህ ማለት አንተ "የተሰራህበት ነገር" እንደማለት ነው፤ ይህ አተረጓጐም ተፈጥሮአዊ ወደ መሆን ቢያደላም፡፡ በርግጥ እያወራን ያለነው በምሳሌ ነው፤ ምክኒያቱም ስለ እግዚአብሔር በተፈጥሮአዊ መንገድ መረዳት አንችልም፡፡ " እግዚአብሔር መንፈስ ነው" (ዮሐንስ 4፡24)፡፡ በተጨማሪም የእግዚአብሔርን ማንነት ከመለኮትነቱ ጋር ማሰብ አለብን። የእግዚአብሔር "ማንነት" ራሱ እግዚአብሔር እንጂ የተለያዩ "አስተዋፅዖዎች" ተቀናብረው አምላክን አልፈጠሩም። 

አካል

ትምህርተ ሥላሴን ስናጠና "አካል" የሚለውን ቃል የምንጠቀመው በዕለት ተለት ኑሮአችን ከምንጠቀምበት በተለየ አግባብ ነው፡፡ ስለዚህ አካል የሚለውን እሳቤ ለትምህርተ ሥላሴ ስንጠቀም ጠንካራ መሠረት ያለው አተረጓጐም ጋር መድረስ ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ ይሆናል።

አካል ስንል ከሌላው ተነጥሎ መኖር የሚችል ልክ እኔ ከሌላው ሰው እንደምለየው "በራሱ የቆመ ግለሰብ" ማለታችን አይደለም። 

በትምህርተ ሥላሴ አግባብ አካል ስንል ራሱን "እኔ" (1ኛ መደብ) ሌላውን ደግሞ "አንተ"(2ኛ መደብ)ብሎ የሚጠራ ማለታችን ነው። ስለዚህ አብ፣ ለምሳሌ፣ ከወልድ ሌላ አካል ነው ምክኒያቱም ራሱን "እኔ" ብሎ ስለሚጠራና ወልድን "አንተ" ብሎ ስለሚጠራው። ስለዚህ በትምህርተ ሥላሴ " አካል" ማለት ከሥላሴ አንዱ ራሱን "እኔ" ብሎ ሲጠራና ሌላውን "አንተ" ሲል ማለታችን ነው፡፡ በሥላሴ ውስጥ የአካል መለያየት የእግዚአብሔር መከፋፈል ሳይሆን "በአንድ ማንነት ነገር ግን በተለያየ የራስ አካል መገኘት" ማለት ነው።

አካልና ማንነት እንዴት ይቆራኛሉ? በማንነትና በአካል መሃል ያለው ግንኙነት እንደሚከተለው ነው። በእግዚአብሔር አንድ የሆነና ያልተከፋፈለ ማንነት ውስጥ ሦስት የአካል "መገለጫዎች" አሉ፡፡ እነዚህ መገለጫዎች የመለኮት ማንነት የሚገኝባቸው አካሎች እንጂ የመለኮት ማንነት ክፍፍሎች አይደሉም። የማንነት ልዩነትና ክፍፍል ሳይኖር የሚገኝባቸው የአካል መገለጫዎች ናቸው፡፡ የስነ መለኮት አዋቂው ሄርማን ባቪንክ እዚህ ላይ እጅግ ጠቃሚ ነገር አስቀምጧል፦ "የሥላሴ አካላት አንድ ማንነት የሚገኝባቸው ሦስት የአካል መገለጫዎች ናቸው፤ በመሆኑም አንድ አካል ከሌላው እንደሚለይ እንዲሁም የሥላሴ አካላት የተለያዩ ናቸው፤ ልክ መዳፍ ምን ጊዜም መዳፍ ቢሆንም የተከፈተ መዳፍ ከተዘጋ መዳፍ እንደሚለየው ማለት ነው።"  

እነዚህ " የአካል መገለጫዎች" የተቆራኙ ስለሆኑ (እያንዳንዳቸው አንድ አካል ስለሆኑ) የራሳቸው የሆነ የህልውና ማዕከል ያላቸው ናቸው፤ በዚህም እያንዳንዱ አካል ራሱን "እኔ" ብሎ ሲጠራ ሌላውን " አንተ'' ብሎ ይጠራል ማለት ነው። ቢሆንም ግን ሦስቱም አካላት አንድ ማንነት አላቸው። የነገረ መለኮት አዋቂውና አቃቤ እምነቱ ኖርማን ጊዝለር እንዳብራራው፣ ማንነት አንተ ምን እንደሆንክ ሲያሳይ አካል ግን ማን እንደሆንክ ያመለክታል። ስለዚህ እግዚአብሔር አንድ "ምን" ነገር ግን ሦስት "እነማን" ነው፡፡

ስለዚህም የመለኮት ማንነት ከሦስቱ የሥላሴ አካላት ''በላይ የሆነ" ወይም "የተነጠለ" ሳይሆን ሦስቱም አካላት ሆነው የተገኙት ማንነት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን የሥላሴ አካላትም በእግዚአብሔር ማንነት ላይ የተጨመሩ ባህሪያት አድርገን መተርጐምም የለብንም። ዋይን ግሩደም እንዳብራራው ፦

"ይሁንና፣ እያንዳንዱ አካል ፍፁም አምላክና የእግዚአብሔር ህላዌ ሁሉ ካለው፣ የአካላቱ ልዩነት በእግዚአብሔር ላይ የተጨመረ (የተደመረ) ባህርይ አድርገን መመልከት የለብንም፤ … ይልቁንም፣ እያንዳንዱ የሥላሴ አካል የእግዚአብሔር ባህሪያት ሁሉ አሉት፤ ሌሎቹ አካላት የሌላቸውን ባህርይ የያዘ አንድም አካል የለም። በሌላ በኩል ደግሞ፣ አካላቱ አማናውያን(እውን) ናቸው፤ የአንዱ እግዚአብሔር ህላዌ የተለያዩ ገጽታዎች አይደሉም፤… ይህንን ለማድረግ ብቸኛው መንገድ ይህ በአካላቱ መካከል ያለው ልዩነት " የህላዌ" ልዩነት ሳይሆን "የግንኙነት " ልዩነት እንደሆነ መገንዘብ ነው፡፡ ይህ እያንዳንዱ ሰብአዊ "ማንነት" የተለየ ህላዌ ከሆነበት ሰብአዊ ተመክሮ እጅግ የተለየ ነው፤ የእግዚአብሔር ህላዌ ግን ከእኛ እጅግ የተለየ ነው፤ በዚህ በአንዱ በማይከፋፈለው ህላዌ ውስጥ ሊከሰት የሚችል የእርስ በእርስ ግንኙነት አለ፤ በመሆኑም ሦስት የተለያዩ አካላት አሉ።"

ትምህርተ ሥላሴን ለማብራራት የምንጠቀምባቸው ምሳሌዎችስ?

ትምህርተ ሥላሴን ለማስረዳት የሚቀርቡ ብዙ ምሳሌዎች አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ጠቃሚ የሆኑ ምሳሌዎች ቢኖሩም፣ የትኛውም ምሳሌ ግን ፍፁም አይደለም። በሌላ አንፃር ግን አንዳንድ ምሳሌዎች ግን ፍፁም ካለመሆን አልፈው ስህተት የሆኑም አሉ። ከነዚህ ምሳሌዎች አንዱ፦  "እኔ ግለሰብ ነኝ፤ ነገር ግን ተማሪም ነኝ፣ ወንድ ልጅ ነኝ፣ ወንድምም ነኝ፤ ይህም እግዚአብሔር አንድና ሦስት ነው የሚለውን ያብራራል" የሚለው ነው። ይህ ሞዳሊዝም የተባለን ኑፋቄ የሚያንፀባርቅ ነው። ይህ ምሳሌ እንደሚለው በርግጥ እግዚአብሔር ሦስት የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት አንድ አካል አይደለም። በሦስት አካል (የህልውና ማዕከል) የሚገኝ አንድ ማንነት ነው እንጂ የሦስት ገጽታዎች መገለጫ አይደለም፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ምሳሌ የሥላሴን ሦስት አካላት ወደ ጐን በመተው እንደ ሦስት ገጽታዎች አድርጐ ያቀርባቸዋል፡፡

ማጠቃለያ

እስከ አሁን ያየናቸውን ሃሳቦች መልሰን በአጭሩ እንቃኛቸው፡፡ 

  1. ትምህርተ ሥላሴ ሦስት አማልክት አሉ አይልም። እግዚአብሔር አንድ ነው፤ እኛም ከዚህ እውነት መሸሽ የለብንም።

  2. ይህ አንድ አምላክ በሦስት አካል ይኖራል።

  3. እነዚህ ሦስት አካላት የአንድ እግዚአብሔር ክፋይ አይደሉም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ የሥላሴ አካል ሙሉ በሙሉና እኩል አምላክ ነው፡፡ በዚህ ባልተከፋፈለ የእግዚአብሔር ማንነት ውስጥ እርስ በርስ የተቆራኘ ግንኙነት ያላቸው ሦስት አካላት አሉ። ይህ የአካል ሦስት መሆን የማንነት መለያየት አይደለም፤ እንዲሁም በዚህ አንድ ማንነት ላይ የሚጨመሩም አይደሉም፤ ነገር ግን ይህ ያልተከፈለ ማንነት በእያንዳንዱ ላይ ሳይከፈል በሙላት የሚገኝባቸው ሦስት አካላት ናቸው። 

  4. እግዚአብሔር ሦስት ገጽታ ያለው አንድ አካል አይደለም። ይህ የሞዳሊዝም ኑፋቄ ነው። አብ ወልድን ከዚያም መንፈስ ቅዱስን አልሆነም። በአንፃሩ በእግዚአብሔር ማንነት ውስጥ ምን ጊዜም ሦስት አካል ነበር፤ ወደፊትም ይኖራል።

  5. ትምህርተ ሥላሴ እርስ በርሱ የሚቃረን አይደለም፤ ምክኒያቱም እግዚአብሔር አንድ የሆነበት መንገድ ሦስት ከሆነበት መንገድ ይለያል። እግዚአብሔር በማንነት አንድ ነው፣ በአካል ሦስት ነው።

ከህይወታችን ጋር ልናዛምዳቸው የምንችላቸው አንዳንድ ነጥቦች

በመጀመሪያ ትምህርተ ሥላሴ አስፈላጊ የሆነው እግዚአብሔርም አስፈላጊ ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር ማን እንደሆነ በሙላት መረዳት እግዚአብሔርን ማክበር ነው፡፡ በተጨማሪም አምልኮአችን ሙሉ እንዲሆን የእግዚአብሔርን ሥሉስነት መቀበል አለብን። የምንኖረውም እግዚአብሔርን ለማምለክ ነው፡፡ እግዚአብሔርም ሰዎች "በመንፈስና በእውነት" (ዮሐንስ4:24) እንዲያመልኩት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህም አምልኮአችንን በእውነትና ከልባችን ለማድረግ መጣር አለብን። 

ትምህርተ ሥላሴ ለፀሎት በጣም ጠቃሚ አተገባበር አለው። አጠቃላዩ የመፅሐፍ ቅዱስ የፀሎት አካሄድ በመንፈስ ቅዱስ ሆኖ በወልድ በኩል ወደ አብ መፀለይ ነው (ኤፌሶን 2፡18)፡፡ ሥሉስ ከሆነ አምላክ ጋር እየተገናኘን እንደሆነ ስናውቅ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ህብረት ያድጋል!

እኛን ከዘላለም ሞት በማዳን ዙሪያ የእያንዳንዱን የሥላሴ አካል ሚና መረዳት የተለየ እረፍት እንዲኖረን፣ በፀሎታችን እግዚአብሔርን የምናመሰግን እንድንሆንና የፀሎት አቅጣጫችንም የተስተካከለ እንዲሆን ይረዳናል። ይሁንና፣ የእያንዳንዱን የሥላሴ አካል ሚና ስንረዳ ይህ ሚና የየራስ ብቻ እንደሆነና የሌላው አካል ተሳትፎ እንደሌለበት አድርገን ማሰብም የለብንም። እንደውም አንዱ አካል የሚያደርገው ሁሉ፣ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ፣ ሌላው ሁለቱም አካል ይሳተፋል፡፡

በጆን ፓይፐር፡፡ © Desiring God. ድረገፅ፦ desiringGod.org

ጆን ፓይፐር በ ሚኒአፖሊስ፣ ሚኒሶታ የቤተልሔም ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ መጋቢ ነው፡፡ ጆን ከፉለር ስነ መለኮት ሴሚናሪ (B.D.) እና ከሙኒክ ዩኒቨርሲቲ (D. theol.) ድግሪዎችን አግኝቷል፡፡ "Let the Nations Be Glad" የተባለውን ጨምሮ ከ30 በላይ መፅሐፍቶች ፀሐፊ ነው። 

 

 

©ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ ኢትዮጵያ። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።