መንፈሳዊ እድገት

መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ማጥናት አለብን?

ሆፕ ግሪፊን እና ታንያ ዋከር

መፅሀፍ ቅዱስን ለመረዳት ፈልገህ ከየትኛው ክፍል መጀመር እንዳለብህ ካላወቅክ ወይም ደግሞ መፅሀፍ ቅዱስ ራሱ ለህይወትህ የሚጠቅም እንደሆነ እያሰላሰልክ ከሆነ ይህ አጭር ትምህርት ይረዳሃል:: ከዚህ በታች ቀለል ባሉ ሦስት ደረጃዎች የተከፋፈሉት መመሪያዎች ቅዱሳት መፅሀፍትን ለማጥናት ቀላል የሆነ ዘዴን ይሰጡሃል:: በወረቀት አትምህ ከመፅሀፍ ቅዱስህ አጠገብ አኑራቸው::

ከየትኛው ክፍል ነው የምጀምረው?

በየትኛውም የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ያለህ መረዳት ጥልቀት እንዲኖረው የሚረዳህ አጠር ያለ ዘዴ እነሆ፤

  1. መመርመር : እግዚአብሔር ምን አለ?

  2. ማቆራኘት :  እግዚአብሔር ምን እያለ ነው?

  3. መተግበር : እግዚአብሔር እየተናገረ ስላለው ነገር ምላሽ የምሰጠው እንዴት ነው?

አንደኛ ደረጃ : መመርመር

በአንደኛው ደረጃ የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍሉ የተፃፈላቸው የመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን እንዴት እንደተረዱት ለመገንዘብ የክፍሉን ዋና ሀሳብ እና ጥቃቅን ደቂቅ ሀሳቦች ትመረምራለህ።

አመላካች የሆኑ ሃሳቦችን ከክፍሉ ላይ ተመልከት።

  • የአጻጻፍ ዘይቤው ምን ዓይነት ነው? ደብዳቤ ነው? ግጥም ነው?

  • በክፍሉ ውስጥ የተጠቀሰው ማነው?

  • በተደጋጋሚ የተጠቀሱ ቃላቶች ወይም ሀረጎች የትኞቹ ናቸው?

  • ክፍሉ ስለ እግዚአብሔር አብ፣ ኢየሱስ ወይም መንፈስ ቅዱስ ምን ይነግርሃል?

እንደ NETBible.ORG ወይም መፅሀፍ ቅዱስህ ላይ ያለውን የማጥኛ ፅሁፍ የመሳሰሉ ተጨማሪ ምንጮች በጥናት ወቅት የሚገጥምህን ክፍተት ለመሙላት ተጠቀማቸው፡፡ እነዚህም ክፍሉ ስለተፃፈበት የመጀመሪያ ቋንቋ ታሪካዊ ወይም ባህላዊ አመጣጥ እንድታውቅ የሚረዱህ እጅግ ጠቃሚ የመረጃ ምንጮች ናቸው፡፡

በዚህም መሰረት በሰበሰብከው መረጃም የደራሲውን ዋና ሃሳብ በአንድ ወይም በሁለት ዓርፍተ ነገር በማጠቃለልና እግዚአብሔር በክፍሉ ውስጥ ምን አለ የሚለውን ጥያቄ በመመለስ አጠቃልል::

ሁለተኛ ደረጃ ፡ ማቆራኘት 

መፅሀፍ ቅዱስ ከረጅም ጊዜ በፊት የተፃፈና የአሁኑ ዘመን አኗኗር ዘይቤ ደግሞ ከዚያ ጊዜ እጅግ የተለየ ቢሆንም የመፅሐፍ ቅዱስ መልዕክት ግን አሁን ድረስ ጠቃሚ (አግባቦት ያለው) ነው:: ነገር ግን በጥናትህ ወቅት በቀድሞው ጊዜና በአሁኑ ጊዜ መሃል የሚገኘውን ክፍተት ማገናኘት ይኖርብሃል::

ማስታወሻ ያዝ፡ በዚያ ጊዜና በአሁኑ ጊዜ መካከል ያሉ በክፍሉ የተጠቀሱ ልዩነቶችን ሁሉ በማወጣት ፃፋቸው:: ከዚያም ተመሳሳይ የሆኑትንም ለይ::

ጠይቅ : ስለመንፈሳዊ ስብራት ክፍሉ ምን ይገልጣል? ክፍሉ ወደ ክርስቶስ እንዴት ያመለክታል? ጊዜ የማይሽራቸውን እውነቶችና መልዕክቶች ከክፍሉ ውስጥ

ለይ: እግዚአብሔር አሁንም ምን እያለ ነው?

ሦስተኛ ደረጃ : መተግበር

አሁን ደግሞ ክፍሉን ወደ ግል ህይወትህ አምጥተህ እግዚአብሔር እየተናገረ ስላለው ነገር ምላሽ የምሰጠው እንዴት ነው የሚለውን ጥያቄ ራስህን ጠይቅ፡፡

ለመፅሀፍ ቅዱስ እውነቶች ራሳችንን ከሰጠን ህይወታችንን የሚቀይሩ ናቸው::

መፅሀፍ ቅዱስ የቱ ጋር እንደተሰበርን ያሳየናል፤ የህይወታችንን እና የልባችንን ትክክለኛ ሁኔታ ገልጦ ያሳየናል::

"12. የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ 13 እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።" ወደ ዕብራውያን  4:12-13

በተጨማሪም እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ወደሰጠን ተስፋና መታደስም ይጠቁመናል፡፡

"14. እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። 15 ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። 16. እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።" ወደ ዕብራውያን  4:14-16

በሁለተኛው የአጠናን ደረጃ ላይ ያገኘኸውን ጊዜ የማይሽረውን መልዕክት መለስ ብለህ ተመልከት፡፡ እግዚአብሔር እኔ ወይም ያለሁበት ማህበረሰብ እርሱ እየተናገረ ላለው ነገር ምላሽ እንድንሰጥ የሚሻው እንዴት ነው የሚለውን ጥያቄ ጠይቅ::

ሞክረው

እነዚህ ሦስት ደረጃዎች ማለትም መመርመር፣ ማቆራኘትና መተግበር በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ ያለህ መረዳት ጥልቅ እንዲሆንና አሁን ባለህበት ህይወት ላይ እንዴት መተግበር እንደምትችል ሊረዱህ ይችላሉ::

ታዲያ በሚቀጥለው ጊዜ መፅሀፍ ቅዱስ ስታነብ ለምን አትሞክራቸውም?

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ በእስር ቤት እያለ የፃፈው አጠር ያለ ደብዳቤ ይህን ለመጀመር ጥሩ ክፍል ነው::

©ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ ኢትዮጵያ። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።