መንፈሳዊ እድገት

በመንፈስ የተሞላ ሕይወት

ዶ/ር ቢል ብራይት

በመንፈስ ቅዱስ የመሞላትን እውቀት ለተረዳና በእያንዳንዱ ጊዜ በእርሱ ምሪት ውስጥ ለሚኖር ክርስቲያን እያንዳንዱ ቀን እጅግ አጓጊና አስደሳች ሊሆንለት ይችላል::
1. ተፈጥሮአዊ ሰው (በራሱ የሚመራ ህይወት)

( ክርስቶስን ያልተቀበለ ሰው)

እኔነት ውሳኔዎችንና ድርጊቶች (በነጠብጣብ የተገለፁትን) እየመራ በዙፋኑ ላይ ተቀምጧል:: ይህም አብዛኛውን ጊዜ ወደ ተስፋ መቁረጥ የሚያመራ ነው:: ኢየሱስ ከዚያ ሰው ህይወት ውጪ ነው::

“ ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።” ( 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡14)


2. መንፈሳዊ ሰው (በክርስቶስ የሚመራ ህይወት)

(ይህ ሰው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራና በድል የተሞላ ህይወት ያለው ሰው ነው)

ኢየሱስ በዚህ ሰው ህይወት ዙፋን ላይ ተቀምጧል:: የሰውየው ማንነት ለኢየሱስ ይገዛል::  በህይወቱም ላይ የኢየሱስ ተፅዕኖና ምሪት አለ::

“መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።” (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች  2 : 15)

3. ስጋዊና ሰው (በራሱ የሚመራ ህይወት)

(ክርስቶስ የተቀበለ ሰው ሆኖ ነገር ግን ክርስትናን በራሱ ጥንካሬ ለመኖር ስለሚሞክር የተሸነፈ ህይወት የሚኖር ሰው)

ኢየሱስ በዚህ ሰው ህይወት ውስጥ ቢኖርም፤ ነገር ግን በዙፋን ላይ አልተቀመጠም፡፡ የሰውየው ማንነትም በዙፋን ላይ ተቀምጦ የህይወቱ  ውሳኔያችንና ድርጊቶችን (በነጠብጣብ የተገለፁትን) ይመራል:: ይህ ግን በስተመጨረሻ ወደ ተስፋ መቁረጥ የሚያመራ ነው::

“እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን?” (1ኛ ቆሮንቶስ 3፡ 1 -3)

 

 እግዚአብሔር የተትረፈረፈና ፍሬያማ ክርስቲያናዊ ህይወት እንደሚኖረን ቃል ገብቶልናል፤ ሰጥቶናልም::

ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- “...እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ፡፡” (ዮሐንስ 10፡10)

“እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና...” (ዮሐንስ 15፡5)

“የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።” (ገላትያ 5፡22-23)

መንፈሳዊ ሰው

በእግዚአብሔር ላይ በመታመን የሚመጡ መንፈሳዊ ባህሪያት:-

 • ክርስቶስን ማማከል

 • በመንፈስ ቅዱስ ሃይልን ማግኘት

 • ለሌሎች ስለክርስቶስ መናገር

 • ውጤታማ የፀሎት ህይወት

 • የእግዚአብሔር ማመንና መታዘዝ

 • ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን ትዕግስትን፣ ቸርነትን፣ እምነትን፣ የዋህነትን፣ በጎነትን እና ራስን መግዛት መለማመድ

እነዚህን ባህሪያት የሚገለጡበት መጠንና ልክ የሚወሰነው ክርስቲያን በእያንዳንዱ የህይወቱ ክፍል ላይ ክርሰቶስን በሚያምንበት መጠንና በክርስቶስ ባለው ብስለት ነው:: የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎትን ገና መለማመድ የጀመረ ሰው ሌሎች ለረዥም ጊዜ በዚህ እውነት የቆዩና የበሰሉ ክርስቲያኖችን በሚመለከትበት ጊዜ እኔ ፍሬያማ አይደለሁም ብሎ  ተስፋ ማጣት የለበትም::

ብዙ ክርስቲያኖች ይህንን የተትረፈረፈ ህይወት የማይለማመዱት ለምንድነው?

ስጋዊ የሆኑ ክርስቲያኖች ይህን የተትረፈረፈና ፍሬያማ ክርስቲያናዊ ህይወት ሊለማመዱ አይችሉም፡፡ ስጋዊ ሰው የክርስትናን ህይወት በግል ጥረቱ ለመኖር የሚታገል ሰው ነው፦

 1. ስለ እግዚአብሔር ፍቅር፣ ይቅርታና ሃይል አያውቅም ወይም ረስቷል:: (ሮሜ 5፡8-10 ፣ ዕብራውያን 10፡ 1-25 ፣ 1ኛ ዮሐንስ 1 ፣ 2፡1 -3 ፣ 2ኛ ጴጥሮስ 1፡9 ፣ ሐዋርያት ሥራ 1፡8 ) 

 2. ከፍና ዝቅ የሚል መንፈሳዊ ልምምድ ያለው ሰው ነው፡፡ 

 3. ራሱን መርዳት ያልቻለ ሰው ነው፡፡ ትክክለኛው ነገር ማድረግ ይሻል፤ ነገር ግን አይችልም፡፡

 4. የክርስቶስን ህይወት ለመኖር እንዴት የመንፈስ ቅዱስ ሀይል መቀበል እንደሚችል አያውቅም፡፡ ( 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡1 -3 ፣ ሮሜ 7፡15 -24 ፣ 8፡7 ፣ ገላትያ 5፡16-18)

ስጋዊ ሰው

እነዚህ ከታች የተጠቀሱት ሁሉም ወይም የተወሰኑት ባህሪያት እግዚአብሔርን በሙሉ ልቡ የማያምንን ክርስቲያን ሊገልጹ ይችላሉ፡-

 • አለማመን
 • አለማታዘዝ
 • ደካማ የፀሎት ህይወት
 • መፅሀፍ ቅዱስን ለማጥናት ያለመፈለግ
 • በልምድ ስርዓት በትችት የተሞላ መንፈስ
 • ንፁህ ያልሆነ አስተሳሰብ፣ ቅናትና የጥፋተኝነት ስሜት
 • ተስፋ መቁረጥ፣ ዓላማ የለሽ መሆን
 • መጨነቅ፣ አቅም ማጣት
 • ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ሰዎች ፍቅር ማጣት

(ክርስቲያን ነኝ እያለ ነገር ግን በተደጋጋሚ በኃጥአት የሚኖር ሰው በ1ኛ ዮሐንስ 2፡3 ፣ 3፡6 ኤፌሶን 5:5 መሰረት መጀመሪያውኑ ክርስቲያን ላይሆን እንደሚችል መረዳት ሊኖርበት ይገባል::);

 

ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ በመሞላት (በመመራትና ሃይል በመቀበል) የሚመጣ የተትረፈረፈና ፍሬያማ ህይወት እንደሚኖረን ቃል ገብቶልናል፡፡

በመንፈስ የተመራ ህይወት ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በእኛ አልፎ የሚኖረው እርሱን ያማከለ ህይወት ነው (ዮሐንስ ወንጌል 15) ፡፡

 1. በዮሐንስ ወንጌል 3:1-8 መሰረት አንድ ሰው ክርስቲያን የሚሆነው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። መንፈስ ቅዱስ ከዚህ ሰው መንፈሳዊ ልደት ጀምሮ ሁልጊዜ በውስጡ ይኖራል (ዮሐንስ ወንጌል 1:12 ፣ ቆላስያስ 2፡9-1ዐ ፣ ዮሐንስ 16፡16-17)፡፡ በሁሉም ክርስቲያኖች ዉስጥ መንፈስ ቅዱስ ቢኖርም ነገር ግን ሁሉም ክርስቲያኖች በመንፈስ የተሞሉ (የሚመሩና ሃይልን የሚቀበሉ) አይደሉም፡፡

 2. መንፈስ ቅዱስ ሞልቶ የሚትረፈረፍ የህይወት ምንጭ ነው (ዮሐንስ ወንጌል 7:37-39)፡፡

 3. መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን ሊያከብር መጥቷል (ዮሐንስ ወንጌል 16፡1-15)፡፡ አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ሲሞላ እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ይሆናል።

 4. ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት በሰጠው የመጨረሻ ትዕዛዝ ለእርሱ ምስክር የመሆን አቅም እንዲኖረን መንፈስ ቅዱስ እንደሚያስችለን ቃል ገብቶልናል (ሐዋርያት ስራ 1፡1-9)፡፡

ታዲያ አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ መሞላት የሚችለው እንዴት ነው?

በመንፈስ ቅዱስ የምንሞላው በእምነት ነው፡፡በዚህም ክርስቶስ ለልጆቹ ሁሉ ቃል የገባላቸውን የተትረፈረፈና ፍሬያማ ህይወት መለማመድ እንችላለን። 

እነዚህን ከታች የተጠቀሱትን ካደረግክ በመንፈስ ቅዱስ ልትሞላ ትችላለህ።

 1. በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላትና ሃይልን ለማግኘት ከልብህ ፈልግ (ማቴዎስ ወንጌል 5:6 ፣ ዮሐንስ ወንጌል 7:37-39)፡፡
 2. ሃጢአትህን ተናዘዝ። በእምነትም እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት በኩል ያለፈውን፣ የአሁኑንና የወደፊቱን ሁሉ ሃጢአትህን ይቅር ስላለህ ምስጋና አቅርብ (ቆላስያስ 2፡ 13-15 ፣ 1ኛ ዮሐንስ 1፣ 2፡1-3፣ ዕብራውያን 1ዐ፡ 1-17)፡፡
 3. ሁሉንም ህይወትህን ለእግዚአብሔር አቅርብ (ሮሜ 12፡1-2)።
 4. የመንፈስ ቅዱስን ሙላት በእምነት ተቀበል።
  • በሚሰጥህ ትዕዛዝ መሰረት በመንፈስ ቅዱስ ተሞላ፡፡ "መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤" (ኤፌሶን 5፡18)።.
  • ተስፋውን ተቀበል፡፡ እንደ ፈቃዱ ስንፀልይ ሁልጊዜ ይመልስልናል፡፡ " በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን።" (1ኛ ዮሐንስ 5፡ 14-15)

እምነት በፀሎት አማካኝነት ሊገለጥ ይችላል…

በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት እንዴት በእምነት መፀለይ እንደሚቻል

በመንፈስ ቅዱስ የምንሞላው በእምነት ብቻ ነው። ነገር ግን እውነተኛ ፀሎት ይህንን እምነትህን የምትገልጥበት አንዱ መንገድ ነው። የሚከተለውን ፀሎት ፀልይ። 

" አባት ሆይ እፈልግሃለሁ። ህይወቴን በገዛ ፈቃዴ ስመራ እንደነበር አውቃለሁ፤ በዚህም አንተን በድያለሁ። ክርስቶስ ስለ እኔ በመስቀል ላይ በመሞቱ ምክኒያት ሃጢአቴን ይቅር ስላልከኝ አመሰግንሃለሁ። አሁንም ክርስቶስ እንደገና በልቤ ዙፋን ላይ እንዲቀመጥ እጋብዛለሁ። ባዘዝኸኝ መሰረት በቃልህ ላይ ሆኜ በእምነት ከጠየቅኩህ እንደምትሰጠኝ ቃል እንደገባህልኝ በመንፈስ ቅዱስ ሙላኝ። ህይወቴን ስለምትመራና በመንፈስ ቅዱስ ስለ ሞላኸኝ አመሰግንሃለሁ።"

ይህ ፀሎት የልብህን መሻት የሚገልፅ ነው? ያ ከሆነ እግዚአብሔር አሁኑኑ በመንፈስ ቅዱስ እንዲሞላህ ጠይቀው። እንደሚያደርገውም እመን።

በመንፈስ ቅዱስ መሞላትህን (መመራትና ሃይል መቀበልህን) እንዴት ማወቅ እንደምትችል

እግዚአብሔርን በመንፈስ ቅዱስ እንዲሞላህ ጠይቀኸዋል? አሁንስ በመንፈስ ቅዱስ መሞላትህን አውቀሃል? በምንስ ስልጣን ነው መሞላትህን ያወቅኸው? (በእግዚአብሔርና በቃሉ ታማኝነት ላይ በመመስረት ነው፡፡ ዕብራውያን 11፡6 ፣ ሮሜ 14፡22-23 ተመልከት)፡፡ 

በስሜትህ ላይ አትመስረት፡፡ በህይወታችን ላይ ስልጣን ሊኖረው የሚገባው የእግዚአብሔር ቃል ተስፋ እንጂ ስሜቶቻችን ሊሆኑ አይገባም፡፡ ክርስቲያን በእግዚአብሔርና በቃሉ ታማኝነት ላይ ባለው እምነት ይኖራል። ይህ የባቡር ምስል በእውነታው (በእግዚአብሔርና በቃሉ) ፣ በእምነታችን (በእግዚአብሔርና በቃሉ ላይ ባለን እምነት) እንዲሁም በስሜቶቻችን (በእምነታችንና መታዘዛችን ምክኒያት በሚመጡት ውጤቶች) መሃል ያለውን ግንኙነት ያሳያል (ዮሐንስ ወንጌል 14፡21) ፡፡

 

በባቡሩ መጨረሻ ላይ ያለው የባቡሩ ሰራተኞች ክፍል ቢኖርም ባይኖርም ባቡሩ ሊጓዝ ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህኛው የባቡሩ አካል ባቡሩን ለመጎተት መሞከር ከንቱ የሆነ ልፋት ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ እንደ ክርስቲያን ህይወታችን በስሜቶቻችን ላይ እንዲደገፍ አናደርግም። ነገር ግን እምነታችን በእግዚአብሔርና በቃሉ ታማኝነት ላይ የተመሰረተ ነው።

በመንፈስ ቅዱስ መመላለስ እንዴት እንደሚቻል

እምነት (በእግዚአብሔርና በሰጠን ተስፋ ላይ ያለን መታመን ) በመንፈስ ለሚመራ ህይወት ብቸኛው መንገድ ነው። በእያንዳንዱ ጊዜ በክርስቶስ ላይ መታመን ስትጀምር፡

 1. ህይወትህ ቀስ በቀስ የመንፈስ ፍሬዎችን ማፍራት ይጀምራል (ገላትያ 5፡22-23)፡፡ ክርስቶስን ወደ መምስልም እየተለወጠ ይሄዳል (ሮሜ 12፡2 ፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 3፡18)፡፡ 

 2. የፀሎት ህይወትህና የመፅሐፍ ቅዱስ ጥናት ጊዜህ ውጤታማ ይሆናል።

 3. በምትመሰክርበት ጊዜ ሃይሉን ትለማመዳለህ ( ሐዋርያት ስራ 1፡8)፡፡ 

 4. ከዓለም ጋር (1ኛ ዮሐንስ 2፡15-17) ፣ ከስጋ ጋር ( ገላትያ 5፡ 16-17) እና ከሰይጣን ጋር (1ኛ ጴጥሮስ 5፡7-9 ፣ ኤፌሶን 6፡1ዐ-13) ለሚገጥምህ መንፈሳዊ ውጊያ ትዘጋጃለህ። 

መንፈሳዊ አተነፋፈስ

በእምነት የእግዚአብሔርን ፍቅርና ይቅርታ መለማመድ መቀጠል ትችላለህ።

ከጌታ ጋር በምታደርገው ጉዞ እርሱን ለማገልገል የሚሻ ቅንነት እያለህ እንኳን በህይወትህ ላይ ጌታን ደስ የማያሰኝ አካሄድና ድርጊት ስታስተውል በመመለስ እግዚአብሔር ያለፈውን፣ የአሁኑንና የወደፊቱን ሃጢአት በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ይቅር ስላለህ አመስግነው። ፍቅሩንና ይቅርታውን በእምነት ተቀብለህ ከእርሱ ጋር ህብረት ማድረግህን ቀጥል። 

ባለመታዘዝ ሃጢአት ምክኒያት የህይወትህን ዙፋን እንደገና ወደ ራስህ ወስደህ ከሆነ ወደ ቀድሞው መንፈሳዊ የአተነፋፈስ ስርዓትህ ተመለስ።

መንፈሳዊ አተነፋፈስ (ቆሻሻውን አውጥቶ ንፁሁን መሳብ) የእግዚአብሔርን ፍቅርና ይቅርታ እንድትለማመድ የሚያደርግህ ልምምድ ነው።

 1. ወደ ውጭ መተንፈስ - ሃጢአትህን ተናዘዝ። በ1ኛ ዮሐንስ 1፡9 እና ዕብራውያን 1ዐ፡ 1-25 መሰረት ከእግዚአብሔር ጋር ተስማምተህ ሃጢአትህን ይቅር ስላለህ አመስግነው፡፡ ሃጢአትን መናዘዝ መመለስንም ያካትታል። ይህም የአመለካከትና የድርጊት ለውጥ ነው።
 2. ወደ ውስጥ መተንፈስ - ህይወትህን በክርስቶስ ቁጥጥር ስር አድርገህ የመንፈስ ቅዱስ ሙላትን በእምነት ተቀበል። በኤፌሶን 5:18 ላይ በተጠቀሰው ትዕዛዙና በ1ኛ ዮሐንስ 5፡14-15 ላይ በተጠቀሰው ተስፋው መሰረት ህይወትህን እርሱ እንደሚመራና ሃይል እንደሚሰጥህ እመን።
   

 


"በመንፈስ የተሞላ ህይወት የሚለውን መረዳት አግኝተሃል?" ከሚለው የካምፓስ ክሩሴድ ፎር ክራይስት አጋር መስራች ከሆኑት ዶ/ር ቢል ብራይት ካዘጋጁት ፅሑፍ ላይ ተጠናቅሮ የተወሰደ። © Cru. All rights reserved.

©ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ ኢትዮጵያ። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።