መፅሐፍ ቅዱስን በግል የማጥኛ ዘዴዎች

ቢል ብራይት

ማርቲን ሉተር መፅሐፍ ቅዱስን የሚያጠናበት መንገድ የአፕል ፍሬን ከሚሰበስብበት መንገድ ጋር አንድ እንደሆነ ተናግሯል።

ዛፉን ሙሉ በአንድ ላይ እንደመወዝወዝ ያህል መፅሐፍ ቅዱስን ሙሉውን በአንዴ ዳስ። በሌላ መፅሐፍ እንደምታደርገው በፍጥነት አንብበው። ከዚያም እያንዳንዱን ዋና ግንድ አወዛውዝ፦ መፅሐፍ በመፅሐፍ አጥና። ከዚያም ለእያንዳንዱ ምዕራፍ ትኩረት እየሰጠህ በማንበብ እያንዳንዱን ቅርንጫፍ አወዛውዝ። ከዚያም እያንዳንዱን አንቀጽና ዓረፍተ ነገር በማንበብ የዛፉን እያንዳንዱን ቀንበጥ አወዛውዝ። ከእያንዳንዱ ቅጠል ስር የቃላቶቹን ትርጉም እየፈለግክ ከተመለከትክ ሽልማትህን ታገኛለህ።

                              

የቶምሰን ቼይን መፅሐፍ ቅዱስ ማጥኛ የሚከተለውን ሃሳብ ያቀርባል፦

መፅሐፍ ቅዱስን ስታነብ ስለአንድ አዲስ ሀገር ጥልቅና ተሞክሮአዊ እውቀት ለማግኘት እንደሚፈልግ ተጓዥ መንገደኛ አንብብ። ሰፊ በሆነው የእውነት ሜዳ ላይ ተጓዝ፤ ከዚያም ወደ ሸለቆው ውረድ፤ ዕይታ ወደምታገኝበት ተራራ ውጣ፣ ውስጥህን የሚያነሳሱትን ወራጅ ውሃዎች ተከተል፤ መመሪያ ወደሚሰጥበት አዳራሽ ግባ፣ አስገራሚ የሆኑትን ጋለሪዎች ጐብኝ ።

ብዙ የአስተምህሮ ስህተቶች የሚመጡት መንፈሳዊ ዕይታን ከማጣት ወይም ጠባብ ከሆነ የመንፈሳዊ እውነት ዕይታ ነው። አዳኛችን ሲናገር፦ "መፃሕፍትንና የእግዚአብሔርን ሃይል አታውቁምና ትስታላችሁ'' ብሏል፡፡

የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገሮች ለማወቅ መሻት ይኑርህ። ማዕድን አውጪ ወርቅ ለማውጣት እንደሚቆፍር፣ ጠላቂ ዋናተኛ ውድ ዕንቁ ለማግኘት ወደ ባህር ጥልቀት እንደሚገባ አንተም ቃሉን እንዲሁ አጥና፡፡

ብዙ ታላላቅ እውነቶች የሚገኙት ላይ ላዩን በማጥናት አይደለም። እነዚህ እውነቶች ወደ ብርሃን የሚመጡት ትዕግስት በሞላበት ጥረት ነው፡፡

እኔና አንተ የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ ስናነብ የእምነት ግምጃ ቤታችንን እየገነባን ነው ማለት ነው። ቃሉን ስናሰላስል እምነታችን እየጨመረ ይሄዳል።

መፅሐፍ ቅዱስን ማንበብ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን መሠረታዊ ነገር ነው። እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ የገለጠበትን ቃሉን ለማንበብ ጊዜን የማንሰጥ ከሆነ ስለ እርሱ መማርና መንፈሳዊ እድገትን እንዴት መለማመድ እንችላለን?

በየቀኑ የተወሰኑ ደቂቃዎችን በመመደብ አንድ ምዕራፍ በማንበብ መጀመር ቀዳሚ እርምጃ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ለመመርመርና በቃሉ ምን እየተናገረን እንደሆነ ለማሰላሰል ረዘም ያለ ጊዜንም መመደብም ያስፈልጋል።

መፅሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ትክክለኛው አመለካከት

ክርስቶስን እንደ ግል አዳኝህን ጌታህ አድርገህ ስትቀበል ታላቅ ጉዞ ጀምረሃል። ይህ ታላቅ ጉዞ በቅዱሳት መፃሕፍት ገፆች ላይ የተፃፈ ነው። መፅሐፍ ቅዱስን በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ስታነብና ስታጠና ለህይወትህ ትርጉም፣ ጥንካሬ፣ አቅጣጫና ሃይልን ትቀበላለህ። እግዚአብሔር የእርሱ ለሆኑት ስላጋጀው ብዙ ታላላቅ የተስፋ ቃሎች ትማራለህ፤ እነርሱንም ትቀበላለህ።

መፅሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ስትመጣ በአክብሮት፣ በመደነቅ፣ አዲስን ነገር በመጠበቅ፣ በፈቃደኛ ልብ፣ እውነትን፣ ፅድቅንና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ሙላት በመጠማት ቅረብ። በትሁትና በተዋረደ ልብ ስትመጣ፤ በርግጥ መንፈስ ቅደስ እውነትን ይገልጥልሃል፤ አንተም የቃሉን የማንፃት ሃይል ትለማመዳለህ።

ከዚህም በላይ የእግዚአብሔርን ቃል ስታነብ ለመታዘዝና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ የምታደርግ የክርስቶስ አምባሳደር መሆንህን በማሰብ ደስ ይበልህ።

ስለመፅሐፍ ቅዱስ ጥናት ምን ይሰማሃል?
 

በዚህ ሰዓት የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት ዋና ምክኒያትህ ምንድነው?
 

ስለመፅሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ጥርት ያለ ግብ አውጥተሃል?
 

አስፈላጊ ግብዓቶች

በመጀመሪያ ቢያንስ ሁለት የመፅሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ዕትሞችን አዘጋጅ፡፡ ባለህበት ቦታ የታተሙ መፅሐፍ ቅዱሶችን ማግኘት አስቸጋሪ ከሆነ በብዙ ቋንቋዎች የተተረጐሙ የመፅሐፍ ቅዱስ ዕትሞችን ለማግኘት ይህንን ድረ ገፅ ተጠቀም፦ www.biblegateway.org

የተለያዩ ትርጉሞችን አጥና። ባለህበት አካላዊ ዓለም እንኳን የአፅናፈ ዓለምን (ዩኒቨርስ) ህጐች ለማወቅ በትጋትና ባለማቋረጥ ማጥናት አለብህ። ታዲያ ይህ ትጋትና ፅናት ሳይኖርህ እግዚአብሔርን ማወቅና ወደር የሌለውን ባለጠግነቱን መረዳት እንዴት ትችላለህ?

ገንዘብ ስታገኝ ደግሞ ቶፒካል መፅሐፍ ቅዱስ ( በርዕስ የተዋቀረ  መፅሐፍ ቅዱስ)፣ ኮንኮርዳንስ (ማጣቀሻ) እና መዝገበ ቃላት መግዛት ሊኖርብህ ይችላል። ተጨማሪ የመፅሐፍ ቅዱስ አጋዥ መፅሐፍት ለጥናትህ የሚረዱህ ስለሚሆኑ በጥናትህ ወቅት ልትጠቀማቸው ትችላለህ። ነገር ግን ጥናትህ ማተኮር ያለበት በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ ነው፡፡ አጋዥ ያልናቸውን መፅሐፍት በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ያዘጋጀልህን እውነት እንድታገኝ የሚረዱህ ብቻ ናቸው፡፡

በእያንዳንዱ ጥናትህ ወቅት የእግዚአብሔርን ቃል በማስታወሻህ ላይ መዝግብ፡፡ ይህን ማድረግህ ጥልቅና እውነተኛ ጥናት እንድታደርግ ከማገዙም በላይ ባጠናኸው ክፍል ላይ እግዚአብሔር ምን እንደተናገረህና የአንተ ምላሽ ምን እንደነበረ የተፃፈ ማሸታወሻ እንዲኖርህ ያደርጋል።

አሁን ያሉህ ግብዓቶች ምንድናቸው?

ተጨማሪ እንዲኖሩህ የምትፈልጋቸውን ግብዓቶች በቅደም ተከተላቸው ዘርዝር።

የሚመከሩ የአጠናን ዘዴዎች

መፅሐፍ በመፅሐፍ ማጥናት፦ መፅሐፍ ቅዱስ በውስጡ ብዙ መፅሐፍትን የያዘ ነው፡፡ ያም ሆኖ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ያዘጋጀውን እኛን የመዋጀት ዕቅዱን በሁሉም መፅሐፍት ውስጥ እናገኛለን። እያንዳንዱ መፅሐፍ የሙሉው መፅሐፍ ቅዱስ አካል እንደሆነ አስብ። በደንብም አንብበው። የሚከተሉትን ምክሮች ከተከተልክ ጥናትህ የተሻለ ትርጉም ያለው ይሆናል፦

  • እግዚአብሔር በቃሉ የተናገረህ ቦታ ላይ አስምር።
  • ዋና ዋና ሃሳቡን ለይ።
  • በመፅሐፉ ውስጥ ያሉት ዋና ዋና ገፀ ባህሪያት አውጣ፤ ማን እንደሆኑና በክፍሉ ውስጥ ያላቸውን ስፍራ ለይ፡፡

  • ከእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ ዋና ዋና ጥቅሶችን በቃልህ ለመያዝና በትንሽ ማስታወሻ ካርድ ላይ መዝግበህ ከራስህ ጋር ሁልጊዜ ለመያዝ ለይተህ አውጣ፡፡

  • መታዘዝ ያለብህን ትምህርቶችና እንድትቀበል የተሰጡህን የተስፋ ቃሎች ዘርዝር::

  • ስለ እግዚአብሔር አብ ፣ ስለ እግዚአብሔር ወልድና ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በመፅሐፉ ውስጥ የተዘረዘሩ ባህሪያት ተመልከት።

እነዚህን ዘዴዎች በመጠቀም ለማጥናት ደስ የሚልህ መፅሐፍ የትኛው ነው? (ከአጫጭሮቹ መፅሐፎች መጀመር ተመራጭ ነው።)  


ምዕራፍ በምዕራፍ ማጥናት ፦ የአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ ዋና ሃሳብ ለማወቅ የሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ በማተኮር አጥና፦

  • የምዕራፉ ዋና ርዕስ ምንድነው?

  • መሪ ትምህርቱ ምንድነው?

  • የምዕራፍ ቁልፍ የሆነው ቁጥር የትኛው ነው? (በቃልህ ያዘው።)

  • ዋና ዋና ገፀ ባህሪዎች እነማን ናቸው?

  • ስለ እግዚአብሔር አብ ምን ያስተምራል?

  • ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያስተምራል?

  • ስለ መንፈስ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

  • ልከተለው የሚገባኝ ምሳሌ አለ?

  • ልርቀው ስለሚገባኝ የተሳሳተ አካሄድ ምን ያስተምረኛል?

  • ማድረግ ስለሚገባኝ ሃላፊነት ምን ያስተምረኛል?

  • እንድቀበለው የተሰጠኝ የተስፋ ቃል አለ?

ከመፅሐፉ ውስጥ አንድ ምዕራፍ ላይ በማተኮር እነዚህን ጥያቄዎች ተግብር።

በአንድ ርዕስ ላይ ያተኮረ ጥናት፦ አንድ ርዕስ በመምረጥ ለምሳሌ፦ ስለ ፀጋ፣ ስለ እውነት፣ ፀሎት፣ እምነት፣ ፅድቅ፣ ዳግም ውልደት ወይም ሰላም የመሣሠሉትን በመምረጥና በርዕስ ዙሪያ የተዋቀረ መፅሐፍ ቅዱስና ማጣቀሻ በመጠቀም የዚያን ርዕስ ሃሳብ ከመላው መፅሐፍ ቅዱስ ላይ በመዳሰስ ተማር።

አንድን ርዕስ ይበልጥ ባጠናህና እና ባዳበርክ ቁጥር ወደተለያዩ ንዑስ ርዕሶች መከፋፈል ይኖርብሃል። ለምሳሌ ስለ ፀሎት ከሆነ የምታጠናው የፀሎት ዓይነቶች፣ የፀሎት የተስፋ ቃሎች፣ በመፅሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ የፀሎት ምሳሌዎች፣ ክርስቶስ ስለ ፀሎት ያስተማረው፣ በፀሎታችን ውስጥ ያለው የክርስቶስ ሚና እና የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የመሣሠሉት ንዑስ ርዕሶች ሊሆኑ ይችላሉ።

በቅድሚያ በምን ርዕስ ዙሪያ ማጥናት ትፈልጋለህ? ለዚህስ ምን ያህል ጊዜ ተመድባለህ?

የግለ ታሪክ ጥናት፦ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ 2,930 ሰዎች ተጠቅሰዋል። የእነዚህን ሰዎች ግለ ታሪክ ማጥናት እጅግ አስደሳች ነገር ነው። በመፅሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ ሰዎች ታሪክ ለምን ይጠቅማል (1ኛ ቆሮንቶስ 1ዐ፡ 11፣ ሮሜ 15፡4)?

ማጣቀሻ፣ በርዕስ የተዋቀረ መፅሐፍ ቅዱስና በመፅሐፍ ቅዱስህ ላይ ያለውን የስም ማውጫ በመጠቀም ማጥናት ስለምትፈልገው ሰው ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጣ።

ማጥናት የምትፈልገውን ሰው ለይ። ለምን እንደመረጥከውም ምክኒያትህን አቅርብና የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ፦

  • ይህ ሰው ይኖርበት የነበረው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

  • ይህ ሁኔታ በህይወቱ ላይ የነበረው ተፅዕኖ ምን ነበር?

  • ስለዚያ ሰው ቤተሰብ ምን የምናውቀው ነገር አለ?

  • በወጣትነቱ ጊዜ ያሳለፈው ልምምድ ምን ነበር?

  • በህይወት ሳለ የፈፀመው ተግባር ምን ነበር?

  • በህይወቱ የገጠመው መጥፎ አጋጣሚ ነበር? ከነበረ ይህ ሰው እንዴት ተጋፈጠው?

  • ዋና ዋና የዚህ ሰው መለያ ባህሪያት የትኞቹ ነበሩ?

  • ጓደኞቹ ማን ነበሩ? ምንስ ዓይነት ሰው ነበሩ?

  • ጓደኞቹ በእርሱ ላይ የነበራቸው ተፅዕኖ ምን ነበር?

  • ህይወቱ የባህርይ እድገት አሳይቷል? ስለ እግዚአብሔር የነበረው ልምምድ ምን ነበር?

  • የፀሎት ህይወቱን፣ እምነቱን፣ እግዚአብሔርን ለማገልገል ያለውን ፍላጐት፣ ለእግዚአብሔር ቃል ያለው ዕውቀት፣ ለመመስከር ያለው ድፍረትንና እግዚአብሔርን ለማምለክ ያለውን አመለካከት ተመልከት።

  • በህይወቱ የሰራቸው ስህተቶች ነበሩ?

  • በህይወቱ ጉልህ የነበር ሃጢአት ነበር?

  • በምን ሁኔታ ሆኖ ነው ይህንን ሃጢአት የሰራው?

  • የዚህ ሃጢአት መልክና በወደፊት ህይወቱ ላይ የነበረው ተፅዕኖስ ምን ነበር?

  • ልጆቹ ምን ይመስሉ ነበር?

  • ለአንተ ህይወት ማደግ የሚጠቅምህ ከዚህ ሰው ህይወት የምትቀስመው ትምህርት አለ?

በዚህ ተከታታይ ትምህርት ላይ የተጠቀሱትን ጥናቶች ከጨረስክ አራቱን የአጠናን ዘዴዎች ተገንዝበሃል ማለት ነው። ለምሳሌ የሐዋርያት ስራን ስላጠናህ የመፅሐፍ ለመፅሐፍ አጠናን ዘዴን ተግብረሃል። ክፍል 2 - ትምህርት 2 እና 4፦ ክርስቲያን እና የተትረፈረፈው ህይወት የሚሉት ደግሞ የምዕራፍ ጥናቶች ናቸው፡፡ እነዚህንና ሌሎች ሁለቱን ዘዴዎችን በግል የመፅሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ወቅት በጥልቀት ለመተግበር በቅርቡ ዝግጁ ትሆናለህ።


በህይወትህ ላይ ለመተግበር የሚረዱህ አቅጣጫዎች

አስቀድሞ ከሁሉም የሳበህ ዘዴ የትኛው ነው?

 

መፅሐፍ ቅዱስን በትኩረት በማጥናትህ ምን ጥቅም የምታገኝ ይመስልሃል?

 

ከአራቱ ዘዴዎች አንዱን ምረጥና በሚቀጥለው ሳምንት ጥናትህ ላይ ተግብረው። ሌሎችን ዘዴዎች ደግሞ በቀጣዮቹ ሳምንታት አድርግ። መፅሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ስትዘጋጅ ሁልጊዜ እርሳስ፣ ማስታወሻ፣ ፀሎትና ትክክለኛው ዓላማ ሊኖርህ እንደሚገባ አስታውስ።

 


ለክርስትና ብስለት የሚረዱ 10 መሠረታዊ ደረጃዎች ከተሰኘውና በካምፓስ ክሩሴድ ፎር ክራይስት አጋር መስራች በሆነው ቢል ብራይት ከተዘጋጀው ፅሑፍ ተጠናቅሮ የተወሰደ። © Cru. All rights reserved.

©ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ ኢትዮጵያ። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።