መንፈሳዊ እድገት

በምትፀልይበት ጊዜ ምን ይሆናል?

ሮስ ማክኮል

 

ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በፀሎት ህይወት ቆይቻለሁ፡፡ በህይወቴ ወሳኝ በነበሩ የለውጥ ጊዜያቶች ላይ እግዚአብሔርን ሳነጋግር አስታውሳለሁ፡፡ 

 • በልጅነቴ የእግዚአበሔርን ህልውና ማመን ስጀምር ፀልዬ ነበር፡፡

 • ኢየሱስን የመከተል ሃሳብ በሚያስጨንቀኝ በአፍላ ወጣትነት ዕድሜዬ ፀልዬ ነበር፡፡

 • ሃይማኖት እንደልቤ እነዳልሆን ገድቦኛል ብዬ እርግፍ አድርጌው በተወኩት ጊዜ እንኳን ፀልዬ ነበር፡፡ 

 • እግዚአበሔር ወደተሻለ ህይወት በጋበዘኝ ጊዜ ፀልዬ ነበር፡፡

 • አዲስ አማኝ፣ አዲስ ባል በተለይ ደግሞ አዲስ አባት በሆንኩባቸው ጊዜያት ፀልዬ ነበር፡፡

ይህንን ሁሉ ስታነብ ፀሎት የተባለውን ነገር ጠንቅቄ የማውቅ እነደሆንሁ ልታስብ ትችል ይሆናል፡፡

ነገር ግን እኔ በክርስትና ህይወቴ ውስጥ ጨርሼ ልረዳቸው ካልቻልኳቸው እና ከሚያሳስቡኝ ነገሮች መሃል በተጨባጭ ላየውና ልሰማው ከማልችለው አምላክ ጋር የሁለትዮሽ ንግግር ማድረግ የሚለው ዋነኛው ነው፡፡ የፀሎት አደራረግ መመሪያ ፅሁፍ የሰጠኝ አንድም ሰው እንደነበርም አላስታውስም፡፡

ማንበብን፣ መፃፍን፣ የሂሳብ ቀመሮችን መስራትን እና ጊታር መጫወትን የተማርኩት በፀሎት ከማሳልፈው ጊዜ እጅግ ባነሰ ጊዜ ነው፡፡ ለመፀለይ ሳስብ ግን ሌሎች በሚገባ ተከታትለውት እኔ ብቻ ሳልገኝ ወደኋላ የቀረሁበት የትምህርት ክፍለ ጊዜ መስሎ የሰማኛል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ጭራሹን እንዴት መፀለይ እንዳለብኝ የረሳሁም ይመስለኛል፡፡

ምን አልባት ይህ ነው የተባለ የራሱ ቀመር ለሌለው ነገር ቀመር እየፈለግኩለት ቆይቼ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ምክኒያት በፀሎት ወቅት ምን አንደሚሆን ለማወቅ ስል አቋራጭ መንገድ ተጠቀምኩ፤ ሚስቴንና ልጆቼን ጠየቅኳቸው።

እነርሱም በፀሎት ወቅት የሚሆነው ነገር ያሉኝንና እኔም የተስማማሁባቸውን ሃሳቦች እነሆ፡-

 • ስትፀልይ አንተ አምላክ እንዳልሆንክ ትገነዘባለህ፡፡

የመፀለይ ፍላጎት ወደ እኛ በመጣ ጊዜ ሁሉ፦ "ላደርግ የምፈልገውን ነገር ሁሉ በራሴ ጥንካሬ ላደርገው አልችልም፡፡ ከእኔ የተሻለና የበለጠ ረዳት ያስፈልገኛል" እያልን ነው፡፡

 • ስትፀልይ ህይወት በአንተ እንደማይጀምርና እንደማያበቃ ትገነዘባለህ፡፡

ህፃናት በሚያለቅሱበት አብዛኛውን ጊዜ ፍላጎታቸው ይሟላላቸዋል። ቀስ በቀስ እድገት እየመጣ ሲሄድ ግን ህይወት በእኛ ዛቢያ እንደማትሽከረከርና እኛ ሁልጊዜ የምንፈልጋት ዓይነት እንዳልሆነች እየተረዳን እንመጣለን፡፡ ለራሳችንም ይሁን ለሌሎች ስንፀልይ ከእኛ የተሻለ ሌላ አካል የአፅናፈ-ዓለም ማዕከል እንደሆነ እውቅና እየሰጠን ነው ማለት ነው፡፡

 • ስትፀልይ ከአንተ ያልመነጨ ጥንካሬን ትላበሳለህ፡፡

ፀሎት ልዕለ ሃያል የሆነ ሃይል በተግዳሮቶቻችን መሃል አብሮን እንዲሆን የምንጋብዝበት ነው፡፡ የትኛውም የእምነት አስተሳሰብ ቢኖረንም ስንፀልይ ጥንካሬን፣ጥበብንና የውስጥ ሰላምና እንደምናገኝ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

 • ስትፀልይ ህይወትህን ሌላ አካል እንዲቆጣጠረው እየሰጠህ ነው፡፡

ሁላችንም በአንድም ይሁን በሌላ መጠን ነገሮችን መቆጣጠር እንፈልጋለን፡፡እንዳንዶቻችን ነገሮችን በመያዝና በመቆጣጠር ከሌሎች የተሻልን እንደሆንን አድርገን እናስባለን፡፡ ፀሎት ግን እግዚአብሔር በህይወታችን የሾፌር መቀመጫ ላይ ሊቀመጥ የተገባው እንደሆነ እንድናምን ያደርገናል፡፡

 • ፀሎት ስለገጠመህ ነገር ትክክለኛውን ስሜትህን እንድታጋራ ይረዳሃል፡፡

እግዚአብሔር ህይወትህን እንዲቆጣጠር ለመስጠት ዝግጁነት ይሰማሃል? በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ከእግዚአብሔር ጋር በግልፅ ተነጋገር፡፡ እርሱ ስለ አንተ ሁሉንም ያውቃል፡፡በሁሉም ጊዜ ሊሰማህ ስለሚጓጓ ፀሎት ሃሳብህንና ስሜትህን ለማወቅና ለማሰላሰል ምቹ ቦታ ይፈጥርልሃል፡፡ 

 • ስትፀልይ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር እንደሆነ ታምናለህ፡፡

መቼም ከወለልና ከጣሪያ ጋር ማውራት ያስደስተኛል ካላልክ በስተቀር ስትፀልይ በርግጥ የሚሰማህ እንዳለና እየፀለይክበት ላለው ነገር ምላሽ እንደሚሰጥህ ማመንህ አየቀርም፡፡

ታዲያ ስለፀሎት ያልኩት ነገር ምን ይመስልሃል? አስፈሪ፣ ሚስጥራዊ፣ ግራ የሚያጋባ?

ፀሎት ሚስጥራዊ ነገር ነው፡፡ ቀላል፤ ነገር ግን በጣም ጥልቅ፡፡ በየቀኑ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ቃላት በፀሎት ይቀርባሉ፡፡ እግዚአብሔር ሁሉንም ይሰማል፡፡ 

አርኪ ከተባለው ልጄ ጋር መፀለይ በጣም ያስደስተኛል፡፡ ለምን? ምክኒያቱም ሲፀልይ እግዚአበሔር እየሰማው እንደሆነ ያምናል፡፡ የእግዚአብሔር መልስ እሺ ይሁን፣ ወይም አይሆንም ይሁን ወይም ደግሞ ጠብቅ የሚልም ቢሆን እሰስኪመልስለት ድረስ ይጠብቃል፡፡

እኔ ወደዚያ አስተሳሰብ ለመድረስ እየሰራሁ ነው፡፡

ምን አልባት አንተም ስትፀልይ እንደ እኔ በፀሎት ዙሪያ ብቁነት አይሰማህ ይሆናል፡፡ ታዲያ ከዚህ በኋላ ምን ታደርጋለህ?

 

©ግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ ኢትዮጵያ። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።